ብልፅግናን መምረጥ የኢትዮጵያን ከፍታ መምረጥ ነው በሚል መሪ ቃል ብልጽግና ፓርቲ በየም ዞን ቶባ ወረዳ የምርጫ ቅስቀሳ እና የድጋፍ ሰልፍ አካሄደ

ብልፅግናን መምረጥ የኢትዮጵያን ከፍታ መምረጥ ነው በሚል መሪ ቃል ብልጽግና ፓርቲ በየም ዞን ቶባ ወረዳ የምርጫ ቅስቀሳ እና የድጋፍ ሰልፍ አካሄደ

በቅስቀሳው ወቅት በፌደራል እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የየም ሕዝብ ተወካይ የሆኑ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች የተሣተፉ ሲሆን የቶባ ወረዳ አመራሮች እና የፖርቲው ደጋፊዎች ቶባ ከተማ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ፤ ብልፅግና ፓርቲ ሀገሪቱን መምራት ከጀመረ ወዲህ በርካታ የልማት ተግባራት ማከናወኑን ተናግረዋል።

እንደ የም ዞን፤ የወረዳዎች መዋቀር እና ምንም ካልነበረበት የከተማ አስተዳደር ከማግኘት በተጨማሪ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ብልፅግና ፓርቲ በዞኑ በልማት ዘርፎች ግቡን አሣክቷል ያሉት አቶ ሽመልስ፤ አሁን የተጀመሩ እና ቀጣይም ለመሥራት የታቀዱ ተግባራትን በብቃት ለማከናወን ብልጽግናን በመምረጥ ድጋፋቸውን መስጠት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የልማት እና የሰላም አርበኛ የሆነው የቶባ ሕዝብም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የቶባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ መኮንን በበኩላቸው፤ ወረዳው ራሱን ችሎ ከወጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰላም፣ በፍትህ እና በመሳሰሉ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ብልጽግናን በማሳካት ረገድ ለውጦች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ስራ ፈላጊ ወጣቶችን በማደራጀት በርካታ ያልታረሰ መሬት በማልማት በወረዳው ሽንኩርት፣ በርበሬ እና መሰል አትክልት እና ፍራፍሬ በማምረት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።

በአካባቢው ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኢንቨስትመንት ዘርፎችም ላይ የተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ብልፅግና ባስቀመጠውን የመሰኖ ልማት ተግባራትን ለማሳለጥ ከባህላዊ የወንዝ እና ምንጭ ጠለፋ በተጨማሪ በከለቺ ቀበሌ ኦዘዋ ወንዝ ላይ 200 ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችል የአምስት ኪሎ ሜትር ካናል ለመሥራት በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ አስተዳደር ድጋፍ በከሪዝ ቀበሌ በ14 ሚሊዮን ብር ወጪ የመስኖ አውታር ለመገንባት የዲዛይን ስራ አልቆ ወደ ተግባር ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ነው ብለዋል።

በወረዳው የማር ምርት በጥራትና በብዛት እየለማ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኤልያስ፤ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፋፊ የእርሻ መሬት በማዘጋጀት የስራ እድል እየተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።

አሁን የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ ለማስቀጠልና ወረዳውን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የወረዳው ነዋሪዎች ለብልጽግና ፓርቲ ድምፃቸውን በመሥጠት ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ማሙዬ ፊጣ – ከወልቂጤ ጣቢያችን