የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የበላይነት ከአውሮፓ ድንበር አልፎ አዲስ ታሪክ ጽፏል።
የዘንድሮው የውድድር ዘመን ለእንግሊዝ ክለቦች ተራ የውድድር ዓመት አይደለም፤ ይልቁንም በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስቱም የአውሮፓ ታላላቅ ውድድሮች የፍፃሜ ወንበርን በአንድ ላይ የተቆጣጠሩበት ድንቅ ወቅት ሆኖ ይመዘገባል።
ታሪኩ የተጀመረው ማክሰኞ ምሽት በለንደን ነው። አርሰናል አትሌቲኮ ማድሪድን በድምር ውጤት 2 ለ 1 በማሸነፍ የሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ትኬቱን በኩራት ቆርጧል።
ሀሙስ ምሽት ደግሞ የእንግሊዝን የበላይነት ይበልጥ ያደመቁ ክስተቶች ተከስተዋል። በኤውሮፓ ሊግ፣ ኡናይ ኤምሪ “የኤውሮፓ ሊግ ንጉስ” መሆናቸውን ዳግም አስመስክረዋል።
አስቶን ቪላ በመጀመሪያው ጨዋታ የደረሰበትን የ 1 ለ 0 ሽንፈት በመቀልበስ፣ ኖቲንግሃም ፎረስትን 4 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት በመቅጣት ግንቦት 12 በኢስታንቡል ከጀርመኑ ፍራይበርግ ጋር ለዋንጫ የሚፋለሙበትን ዕድል አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ ሰዓት በደቡብ ለንደን፣ ክሪስታል ፓላስ የዩክሬኑን ሻክታር ዶኔትስክን በሁለተኛው ዙር 2 ለ 1 በማሸነፍ (በድምር ውጤት 5 ለ 2) በኮንፈረንስ ሊግ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍፃሜ ደርሷል። ፓላሶች ግንቦት 19 ከስፔኑ ራዮ ቫሌካኖ ጋር ለታሪካዊ ዋንጫ ይፋለማሉ።
እንግሊዝ ከዚህ ቀደም በ 2019 እና በ 2021 በአውሮፓ መድረክ ደምቃ ታይታለች። በተለይም በ 2019 ሊቨርፑል ከቶተንሃም፣ ቼልሲ ከአርሰናል ጋር ያደረጉት የፍፃሜ ጨዋታ አይረሳም።
ይሁን እንጂ ሦስቱንም የፍፃሜ መድረኮች በአንድ ዓመት መርገጥ ለሀገሪቱ የሁልጊዜም ህልም ሆኖ የቆየ ስኬት ነው።
ይህንን ስኬት ቀደም ብለው ያስመዘገቡ ሀገራት ጥቂት ናቸው። በተለይም ጣሊያን በ 1990ዎቹ ወርቃማ ዘመኗ በ 1989-90 የውድድር ዘመን ሦስቱንም ዋንጫዎች (በኤሲ ሚላን፣ ጁቬንቱስ እና ሳምፕዶሪያ አማካኝነት) በመውሰድ የምትጠቀስ ናት። ስፔንም በ 1985-86 ተመሳሳይ ሙከራ አድርጋ ነበር።
ጣሊያን በሁሉም የሚገኙ የአውሮፓ የፍፃሜ ውድድሮች ላይ ተወካይ ማግኘት በተደጋጋሚ ተሳክቶላታል፤ በቅርብ ጊዜም በ2023 ይህንኑ አሳክታ ነበር።
ይሁን እንጂ ክለቦቿ በሦስቱም የፍፃሜ ጨዋታዎች ተሸንፈዋል – ኢንተር ሚላን በሻምፒዮንስ ሊግ፣ ሮማ በኤውሮፓ ሊግ እንዲሁም ፊዮሬንቲና በኮንፈረንስ ሊግ ተሸናፊ ሆነዋል።
ከሊቨርፑል የ 1981 እና 1984 ድሎች በኋላ፣ እንግሊዝ በአውሮፓ መድረክ እንዲህ ያለ ሰፊ የበላይነት ያሳየችበት ወቅት አልነበረም።
አሁን የቀረው አንድ ጥያቄ ብቻ ነው፡- እንግሊዝ ሦስቱንም ዋንጫዎች ጠቅልላ በመውሰድ እንደ ጣሊያን ታሪክ ትደግም ይሆን?
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
በዛሬው ዕለት የተሰሙ የዝውውር መረጃዎች
በስፖርቱ ዘርፍ እየተደረገ ያለዉ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለጸ
ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ማይክል ኦሊሴ ላይ ዓይናቸውን ጣሉ!