ከባርሴሎናው ጥላ ስር እስከ አውሮፓው የክብር ማማ
ከዛሬ 27 ዓመታት በፊት በካታላኑ ኩራት ካምፕ ኑ ስታዲየም ቅጥር ግቢ ውስጥ ሁለት ወጣቶች ነበሩ። አንደኛው የባርሴሎናው ዋና ቡድን የልብ ትርታና መሪ የሆነው ሉዊስ ኤንሪኬ ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ በታዋቂው ላማሲያ አካዳሚ ውስጥ እንደ አልማዝ እየተቀረጸ የነበረውና የነገውን ብሩህ ተስፋ ሰንቆ በባርሴሎና “ቢ” ቡድን ውስጥ የሚንከላወሰው ታዳጊው ሚኬል አርቴታ ነበር።
ያኔ አንዱ ለሌላው ምሳሌ፣ አንዱ የሌላው አድናቂ ነበሩ። ዛሬ ግን ጊዜው ተለወጠ፤ ዓመታት ነጎዱ። ያ ታዳጊ ዛሬ ጎልምሶ፣ ያ አንጋፋ ደግሞ በልምድ በዝቶ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ መድረክ ላይ ፊት ለፊት ተፋጠዋል።
የእግር ኳስ አምላክ እንዲህ አይነቱን አስገራሚ ትዕይንት የሚጽፈው በጥንቃቄ ይመስላል።
በ1990ዎቹ ማብቂያ አካባቢ ኤንሪኬ በካታላኑ ቤት የኃይልና የጥበብ ምንጭ በነበረበት ወቅት፣ አርቴታ በላማሲያ የፔፕ ጋርዲዮላን ፈለግ ለመከተል የሚተጋ “የነገው ኮከብ” ተብሎ የሚጠበቅ ወጣት ነበር።
አርቴታ በወቅቱ ስለ ኤንሪኬ ሲናገር “በእግር ኳስ ሜዳ ላይ ያለውን ስብዕናና ለቡድኑ የሚሰጠውን መስዋዕትነት ሁሌም አደንቃለሁ” ይል ነበር።
በውድድሩ ፍፃሜ ታሪክ ከአንድ ሀገር የመጡ አሰልጣኞች በፍፃሜው ሲገናኙ ይህ ለአራተኛ ጊዜ ሆኗል።
ከዚህ በፊት በፈረንጆቹ 2003 ጣልያናዊያኑ ካርሎ አንቾሎቲ ( ኤሲ ሚላ ) እና ማርሴሎ ሊፒ ( ጁቬንቱስ ) 2013 ፣ጀርመናውያኑ ጁፕ ሀይንኬስ ( ባየር ሙኒክ ) እና የርገን ክሎፕ ( ዶርትመንድ ) ፣በ2020 ጀርመናዊያኑ ሀንሲ ፍሊክ ( ባየር ሙኒክ ) እና ቶማስ ቱሄል ( ፒኤስጂ ) መገናኘታቸው ይታወሳል።
ሉዊስ ኤንሪኬ እና ሚኬል አርቴታም በታሪክ መፅሐፍ ላይ ይህንን ጥምረት ቡዳፔስት ላይ ይቀላቀላሉ።
ዛሬ የሁለቱ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ሉዊስ ኤንሪኬ በልምድ የካበተ፣ ሻምፒዮንስ ሊግን በባርሴሎና ቤት በመሪነት ያሸነፈና “ታክቲካዊው አውሬ” ተብሎ የሚጠራ አሰልጣኝ ሆኗል።
በሌላ በኩል ሚኬል አርቴታ፣ የሰሜን ለንደኑን መድፈኞች ከነበሩበት ድባብ አውጥቶ፣ በአዲስ አስተሳሰብና በጠነከረ ስነ-ልቦና አንበሳነታቸውን አስመስክሮ ለፍጻሜው አብቅቷል።
ይህ ጨዋታ በሜዳ ላይ በ11 ተጫዋቾች መካከል የሚደረግ ፍልሚያ ብቻ አይደለም። ይህ ጨዋታ የሁለት የባርሴሎና ፍልስፍና ውጤቶች፣ የሁለት ትውልዶች እና የሁለት ታላላቅ አእምሮዎች ቼዝ ነው።
ከ27 ዓመታት በፊት አንዱ ለሌላው አርአያ ነበር፤ ዛሬ ግን ሁለቱም ለክብሩ ሲሉ የሞት ሽረት ፍልሚያ ያደርጋሉ።
ታሪክ ራሱን ይደግማል ወይስ አዲሱ ታሪክ ይጻፋል? መላው ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው ታሪካዊው የአሰልጣኞች ፍልሚያ!
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የቡዳፔስቱ ቀጠሮ
“አስተናጋጃችን ፊፋ ነው እንጂ ትራምፕ አይደሉም!” – ኢራን
አርሰናል የእንግሊዝ ባለጸጋ ለመሆን ተቃርቧል!