እግር ኳስ የሰከንድ ስብርባሪዎች ድምር ውጤት ነው። ነገር ግን በአንዳንድ ሰዎች እጅ ያ ሰከንድ ወደ ዘላለምነት ይቀየራል።
በፈረንጆቹ ግንቦት 2013 ልክ በዛሬዋ ዕለት በመላው ዓለም የሚገኙ የስፖርት አፍቃሪዎችን ልብ ለአፍታ ያቆመ ያ አስደንጋጭ ግን ደግሞ የሚጠበቅ ዜና ከኦልድ ትራፎርድ ተሰማ።
የጥቁር መጋረጃው ተከፈተ፣ ታሪካዊው መሪ በትረ ስልጣናቸውን አስቀመጡ።
ለ26 ረጅም ዓመታት በኦልድ ትራፎርድ የቴክኒክ ሳጥን ውስጥ እንደ ንስር ሲያማትሩ የነበሩት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን፣ ከሜዳ ውጭ መሆናቸውን አበሰሩ።
ይህ ዜና የአንድ ሰው ጡረታ መውጣት ብቻ አልነበረም፤ የዘመን መለወጫ እንጂ። በ1,500 ጨዋታዎች ላይ ቡድናቸውን የመሩት ፈርጉሰን፣ 895 ጊዜ የድልን ጽዋ ከተጎነጩ በኋላ ማሰልጠን በቃኝ አሉ።
ብዙዎች ‘የማይቻል’ የሚሉትን ታሪክ በደም እና በእንባ ጽፈዋል። 38 የክብር ጽዋዎች! 13 የፕሪምየር ሊግ ዋንጫዎች፣ 2 የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ስፍር ቁጥር የሌላቸው የአገር ውስጥ ዋንጫዎች።
ሰር አሌክስ ማንቸስተር ዩናይትድን ከሊቨርፑል ጥላ ስር አውጥተው፣ የእንግሊዝ እግር ኳስ የበላይ እንዲሆን አስችለዋል።
በአንድ ወቅት ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ የእኔ ትልቁ ፈተና ሊቨርፑልን ከከፍታቸው ላይ ማውረድ ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል። ያሉትንም በተግባር አሳይተዋል።
ዛሬ ላይ ሆነን ያንን ቀን ስናስታውስ፣ ፈርጉሰን ያሸነፏቸው ዋንጫዎች ብቻ ሳይሆኑ የገነቧቸው ስብዕናዎች ይገርሙናል። ከዴቪድ ቤካም እስከ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ከራያን ጊግስ እስከ ፖል ስኮልስ፤ እሳቸው ጋዜጠኞችን የሚያስጨንቁ፣ ዳኞችን የሚያስፈሩ፣ ግን ደግሞ ለተጫዋቾቻቸው እንደ አባት የሆኑ ታላቅ መሪ ነበሩ።
ታሪክ ይዘከራል፣ ስም ግን ይኖራል። ሰር አሌክስ ፈርጉሰን – የእግር ኳስ ታሪክ የማይረሳቸዉ ሰዉ ናቸዉ!
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ አስፈረመ
ማንቸስተር ዩናይትድ አንድሬ ሳንቶስን አስፈረመ
የ2018 የCBE የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በማሸነፍ ሁለት ዋንጫ ላነሳው የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ክልሉ ያዘጋጀውን የዕውቅናና የሽልማት ፕሮግራም ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 06/2018 ከቀኑ 12፡00 ጀምሮ በሀዋሳ ሀይሌ ሪዞርት ይካሄዳል።