የበቆሎ ምርጥ ዘር በወቅቱ በማግኘታቸው ትኩረታቸውን የእርሻ ዝግጅት ላይ እንዲያደርጉ እንዳስቻላቸው በጉራጌ ዞን የአበሽጌ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ
ለበልግ እርሻ 7 ሺህ 500 ኩንታል የበቆሎ ምርጥ ዘር ለእርሶ አደሮች ማከፋፈሉን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ገልጿል።
በወረዳው ምችሌና ጠረቆ እንዲሁም ቱባና ተሊሎ ቀበሌዎች ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች፤ የበቆሎ ምርጥ ዘር በወቅቱ በማግኘታቸው ትኩረታቸውን የበልግ እርሻ ዝግጅት ላይ እንዲያደርጉ ማስቻሉን ተናግረዋል።
አያይዘውም የነዳጅ እጥረት በቂ የትራክተር አገልግሎት እንዳያገኙ በማድረጉ ከባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክረ ሀሳቦች ተቀብለው ደቦና የቤተሰብ ጉልበት እንዲሁም በበሬ ተጠቅመው ማሳዎቻቸውን ለዘር በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል እርሶ አደሮቹ።
በወረዳው የቱባና ተሊሎ ቀበሌ ልማት ጣቢያ አስተባባሪና ባለሙያ አቶ ጌትነት አስማረ ከባልደረቦቹ ጋር በጋራ በመሆን ለአርሶ አደሮች ሙያዊ ድጋፍ ከመስጠት ጎን ለጎን ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን እንዲሁም ባህላዊና ዘመናዊ የእርሻ አማራጮች ተጠቅመው የማሳ ዝግጅት እንዲያደርጉ በመቀስቀስ ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
የአበሽጌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም ናስር፤ ለበልግ እርሻ 7 ሺህ 500 ኩንታል ሊሙ የበቆሎ ምርጥ ዘር ለእርሶ አደሮች ማከፋፈላቸውን አስረድተዋል።
በወረዳው በ2018 ምርት ዘመን 41 ሺህ 605 ሄክታር ማሳ በተለያዩ ሰብሎች ለማልማት እየተሰራ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንድ ሺህ 50 ሄክታር በሩዝ እንዲሁም 14 ሺህ 986 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 38 ሺህ ሄክታር በበቆሎ ሰብል ለመሸፈን ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ የተናገሩት ሀላፊው፤ ይህንን ማሳ ለማሳረስ ከ76ዐ ሺህ ሊትር በላይ ናፍጣ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ በነዳጅ አቅርቦት ላይ የተፈጠረው እጥረት በበልግ እርሻ ዝግጅቱ ላይ የሚያሳድረው ጫና እንዳይሰፋ አርሶ አደሩ የበሬዎች እና የጋማ ከብቶችን ጨምሮ ሁሉንም የእርሻ አመራጮች ተጠቅሞ የማሳ ዝግጅቱን እንዲያጠናከር በመስራት ላይ እንደሚገኙና በዚህም 550 ሄክታር መሬት መታረሱንም ገልፀዋል።
ወረዳው ለበልግ እርሻ 185 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልገው የተናገሩት አቶ አብድልከሪም፤ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በእጃቸው የገባው 42 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የባስኬቶ ዞን ላስካ ዙሪያ ወረዳ ህዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 10ኛ አመት የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል
የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምክር ቤቶች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባቸው የኮንሶ ዞን ህዝብ ምክር ቤት ገለጸ
የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ አሳታፊ እና የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ