የቡዳፔስቱ ቀጠሮ

የቡዳፔስቱ ቀጠሮ

የአውሮፓ እግር ኳስ ማማ… የክለቦች ሁሉ ቁንጮ በሆነው ሻምፒየንስ ሊግ፣ የፈረንሳዩ ሀብታም ክለብ ፒኤስጂ በድጋሚ ታሪክ ጽፏል! በባቫርያው ግዙፍ ባየር ሙኒክ ላይ የደረሰውን ከባድ ፈተና ተቋቁመው ፓሪስያውያኑ ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት የፍፃሜውን ትኬት ቆርጠዋል።

ትላንት ምሽት በባየር ሙኒክ የመልስ ጨዋታ፣ ሜዳውም መንፈሱም ለባቫርያኑ የሚያደላ ቢመስልም፣ የሉዊስ ኤንሪኬው ስብስብ ግን የብረት መጋረጃውን ጥሶ አልፏል።

ጨዋታው 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ቢጠናቀቅም ፒኤስጂ በመጀመሪያው ጨዋታ በነበረው ብልጫ ታግዞ በድምር ውጤት 6 ለ 5 በሆነ ጠባብ ግን ጣፋጭ ድል ወደ ፍፃሜው አምርቷል።

ኡስማን ዴምቤሌ የፓሪስን ደጋፊዎች ያስፈነጠዘች ድንቅ ጎል ሲያስቆጥር፤ እንግሊዛዊው የጎል ማሽን ሀሪ ኬን ለባየር ሙኒክ የአቻነት ግብ ቢያስቆጥርም ሙኒክን ከሽንፈት ሊታደጋት አልቻለም።

ይህ ውጤት ፒኤስጂ ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት ለፍፃሜ እንዲደርስ ከማድረጉም በላይ ክለቡ ለአውሮፓ ትልቅ ክብር ያለውን ጥማት ዳግም አሳይቷል።

አሁን ሁሉም አይኖች ወደ ሀንጋሪው ቡዳፔስት ያማትራሉ። ፒኤስጂ በታሪካዊው የፑሽካሽ አሬና ስታዲየም ከእንግሊዙ መድፈኞች… ከአርሰናል ጋር ለዋንጫ ይፋለማሉ።

ይህ ጨዋታ ለሉዊስ ኤንሪኬ እና ለሚኬል አርቴታ ትልቅ የስትራቴጂ ፍልሚያ፣ ለደጋፊዎች ደግሞ የማይረሳ የግርግር ምሽት እንደሚሆን ይጠበቃል።

የቀድሞው የሜዳው ጀግና አርቴታ እና በከዋክብት የተገነባው የፓሪሱ ስብስብ የሊጉን ዋንጫ ለመሳለም ፊት ለፊት ተፋጠዋል::

የአውሮፓ እግር ኳስ ከፍተኛው ክብር የሆነው የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ በዚህ ወር መጨረሻ በሀንጋሪ መዲና ቡዳፔስት አዲሱን ንጉስ ለመቀበል ዝግጅቷን አጠናቃለች።

ይህ ፍጻሜ ዝም ብሎ የእግር ኳስ ጨዋታ ብቻ አይደለም፤ የአርሰናል የዓመታት የናፍቆት ጉዞ እና የፒ.ኤስ.ጂ የሀብትና የክብር ጥያቄ የሚገናኙበት ታሪካዊ መድረክ ነው።

አርሰናል ካለፉት መራራ ዓመታት በኋላ አሁን በወጣት ከዋክብቱ ታጅቦ ለፍጻሜ መቅረቡ ለብዙዎች አስገራሚ ሆኗል።

ሚኬል አርቴታ የገነባው ይህ ስብስብ፤ በሜዳ ላይ የሚያሳየው የታክቲክ ስነ-ስርዓት እና የማይበገረው የአሸናፊነት መንፈስ ለለንደኑ ክለብ አዲስ ተስፋን ሰጥቷል። ክለቡ ከዓመታት በፊት በፓሪስ ያመለጠውን ይህን ትልቅ ዋንጫ አሁን በቡዳፔስት ምሽት ለመበቀል እና ታሪክ ለመስራት ቆርጦ ተነስቷል።

በሌላ በኩል የአውሮፓን ክብር በብርቱ የሚሹት የፓሪስ ሴንት ዠርሜን ተጫዋቾች፣ ይህንን አጋጣሚ ለምንም አሳልፈው መስጠት አይፈልጉም።

በከዋክብት የተሞላው የፓሪሱ ስብስብ በግለሰብ ብቃት የታጀበ ድንቅ እግር ኳስን እያሳየ ወደ ፍጻሜው መጥቷል። ለፒ.ኤስ.ጂ ይህ ዋንጫ ከስኬት በላይ ትርጉም አለው፤ በአውሮፓ መድረክ ያላቸውን የበላይነት ለማረጋገጥ የሚጠቀሙበት የመጨረሻው ቁልፍ ነው።

በሜዳ ላይ የሚታየው ትንቅንቅም እጅግ ተጠባቂ ነው። የአርሰናል የማጥቃት ስልት እና የተከላካዮቹ ጥንካሬ ከፒ.ኤስ.ጂ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እና የፊት መስመር ከዋክብት ጋር ሲገናኝ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

ቡዳፔስት የሁለት የተለያዩ የእግር ኳስ ፍልስፍናዎች መጋጠሚያ ትሆናለች።

አርሰናል የመጀመሪያውን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ወደ ኤምሬትስ ይወስዳል ወይስ ፒ.ኤስ.ጂ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ሻምፒዮን ይሆናል? የዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጠው በቡዳፔስት የፍጻሜ ምሽት ይሆናል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ