“አስተናጋጃችን ፊፋ ነው እንጂ ትራምፕ አይደሉም!” – ኢራን

“አስተናጋጃችን ፊፋ ነው እንጂ ትራምፕ አይደሉም!” – ኢራን

የሜዳው ፉክክር ወይስ የፖለቲካው ትንቅንቅ? ኢራን ለአሜሪካ “ቅድመ ሁኔታ” አስቀመጠች፡፡

የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሊጀመር ጥቂት ሳምንታት ቢቀሩትም፣ ከሜዳው ውጭ ያለው የቃላት ጦርነት ግን ከአሁኑ ደርቷል።

በኳስ አፍቃሪው ዘንድ “የሞት ምድብ” ተብሎ የሚጠራው ሳይሆን፣ በዲፕሎማሲው ዓለም “የመከራ ምድብ” የሆነው የኢራን እና የአሜሪካ ፍጥጫ አዲስ ምዕራፍ ይዟል።

የኢራን እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ፕሬዝዳንት መህዲ ታጅ፤ ወደ አሜሪካ ለሚያደርጉት ጉዞ እጅግ ጠንካራና አነጋጋሪ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል።

ባለፈው ሳምንት በካናዳ ድንበር ላይ የደረሰባቸውን “የቪዛ ስረዛና እንግልት” ተከትሎ ታጅ ለሀገራቸው ብሔራዊ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ  “እኛ ወደ ዓለም ዋንጫው የምንሄደው በብቃታችን አልፈን ነው። አስተናጋጃችን ደግሞ ፊፋ ነው እንጂ አቶ ትራምፕ ወይም አሜሪካ አይደሉም።” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ በተለይም የኢራን አብዮታዊ ዘበኛ (IRGC) ክብር የማይጠበቅ ከሆነና ለባለስልጣኖቻቸው ዋስትና የማይሰጥ ከሆነ፣ የቡድኑ ተሳትፎ በጥያቄ ምልክት ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።

የውዝግቡ መነሻ ባለፈው ሳምንት በቫንኩቨር በተካሄደው የፊፋ ኮንግረስ ላይ ኢራን ሳትገኝ መቅረቷ ነው።

መህዲ ታጅና ልዑካቸው በአየር ላይ እያሉ የካናዳ መንግስት ቪዛቸውን የሰረዘው ከኢራን አብዮታዊ ዘበኛ (IRGC) ጋር ንክኪ አላችሁ በሚል ሲሆን፤ ይህ ተቋም ደግሞ በአሜሪካና በካናዳ በ”አሸባሪነት” የተፈረጀ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ ከዚህ ቡድን ጋር ግንኙነት ያለው ማንኛውም ግለሰብ ወደ አሜሪካ ምድር እንደማይረግጥ በቁርጥ ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ በሎስ አንጀለስና በሲያትል ጨዋታዎቿን ለምታደርገው ኢራን ትልቅ አዳጋ ሆኖባታል።

የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በበኩላቸው፤ ኢራን በተያዘላት መርሃ-ግብር መሰረት በአሜሪካ ጨዋታዎቿን እንደምታደርግ በልበ ሙሉነት እየተናገሩ ነው።

ሆኖም ኢራን “ጨዋታዎቼ ወደ ሜክሲኮ ይዛወሩልኝ” ስትል ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ መደረጉና በምትኩ በመጪው ግንቦት ወር በዙሪክ ለሚደረገው አስቸኳይ ስብሰባ መጠራቷ ውጥረቱን አላረገበውም።

በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ፖለቲካና ስፖርት ተቀላቅለው አያውቁም ቢባልም የዘንድሮው የሰሜን አሜሪካ ዓለም ዋንጫ ግን ገና ሳይጀመር በጂኦ-ፖለቲካ ማዕበል እየተናወጠ ይገኛል።

የኢራን ብሔራዊ ቡድን በሎስ አንጀለስ ሜዳ ላይ ይገኛል ወይስ የዲፕሎማሲው ፍጥጫ ኳሷን ሳይመታ ያስቀራታል? ለሚለው ጥያቄ የፊፋና የዋሽንግተን ቀጣይ እርምጃ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ