አርሰናል የእንግሊዝ ባለጸጋ ለመሆን ተቃርቧል!

አርሰናል የእንግሊዝ ባለጸጋ ለመሆን ተቃርቧል!

ከሜዳ ላይ ድል እስከ ካዝና ሙላት፤ የሰሜን ለንደኑ መድፈኞቹ አርሰናል በታሪካቸው አዲስ ምዕራፍ እየከፈቱ ይገኛሉ።

ለዓመታት ከታላላቅ ስኬቶች ርቀው የቆዩት መድፈኞቹ አሁን ላይ ግን በሜዳ ላይ በሚያሳዩት አስደናቂ ብቃት የታጀበ የገንዘብ ዝናብ እየዘነበላቸው ይገኛል።

አርሰናል ሊቨርፑልን እና ማንቸስተር ሲቲን በመብለጥ የኢንግሊዝ ቁጥር አንድ ባለጸጋ ክለብ ለመሆን ጥቂት እርምጃዎች ብቻ ቀርተውታል።

ባለፈው የ2024/25 የውድድር ዘመን ክለቡ የ691 ሚሊየን ፓውንድ የገቢ ሪከርድ ማስመዝገቡ ይታወሳል። ይሁን እንጂ የዘንድሮው ጉዞ ያንን ታሪክ ድባቅ የሚመታ እንደሚሆን ይገመታል።

እንደ ስካይ ስፖርት ዘገባ ከሆነ የንግድ ገቢ በ41 በመቶ እድገት አሳይቶ 263 ሚሊየን ፓውንድ ደርሷል።

የስታዲየም ገቢ በ154 ሚሊየን ፓውንድ ወይም 17 በመቶ  እድገት አሳይቷል፡፡ከስርጭት መብት ደግሞ 213 ሚሊየን ፓውንድ ወደ ካዝናው ገቢ ሆኗል።

የአርሰናል ወደ አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ መጓዝ ለደጋፊዎቹ ደስታን ብቻ ሳይሆን ለክለቡ አስተዳደርም ትልቅ የገንዘብ በረከትን ይዟል።

መድፈኞቹ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ድረስ ባደረጉት ጉዞ ብቻ 122 ሚሊየን ፓውንድ ገቢ ማግኘታቸው ተረጋግጧል።ይህ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ደረጃ ጋር ሲነጻጸር የ21 ሚሊየን ፓውንድ ብልጫ አለው።

የፍፃሜውን ጨዋታ ማሸነፍ ደግሞ ተጨማሪ 10 ሚሊየን ፓውንድ ከማስገኘቱም በላይ በ2029 ለሚካሄደው የዓለም የክለቦች ዋንጫ  ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።ይህም እንደ ቼልሲ ሁሉ ተጨማሪ 90 ሚሊየን ፓውንድ የሚያስገኝ ወርቃማ ዕድል ነው።

ይህ ለአርሰናል ዝም ብሎ ስኬት አይደለም የኃይል ሚዛን ሽግግር ነው ይላሉ የስፖርት ፋይናንስ ባለሙያዎች።

አርሰናል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ ከቻለ ካለፈው ዓመት የ2ኛ ደረጃ ክፍያ (£171.5m) በላቀ ሁኔታ የሊጉ ከፍተኛ ተከፋይ በመሆን ንግስናውን ያውጃል።

መድፈኞቹ በሜዳ ላይ የሚረጩት ጥበብ በለንደን ሰማይ ስር የገንዘብ ማማ እየገነባላቸው ነው።

ጥያቄው አርሰናል ይህንን የፋይናንስ የበላይነት ተጠቅሞ ለስንት ዓመታት በእንግሊዝ እግር ኳስ አናት ላይ ይቆይ ይሆን? የሚለው ነው።

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ