ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባሻገር በውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ ኃላፊነት በመስጠት ሀገራዊ ራዕይ እያሳካ እንደሚገኝ በኣሪ ዞን የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ አባላት ገለፁ

ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩ ባሻገር በውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ ኃላፊነት በመስጠት ሀገራዊ ራዕይ እያሳካ እንደሚገኝ በኣሪ ዞን የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ አባላት ገለፁ

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ አባላት በጂንካ ከተማ የእግር ጉዞና በምክር ቤት አዳራሽ ለፓርቲው ያላቸውን ድጋፍ በገለፁበት ወቅት ነው ይህንን የገለፁት።

የኣሪ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የሴቶች ክንፍ ኃላፊ ወ/ሪት ይመኙሻል ተፈሪ እንደገለፁት፤ ፓርቲው ለሴቶች በርካታ ዕድሎችን በማመቻቸት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተጨባጭ ውጤት እንዲመዘገብ አድርጓል።

ይህ ውጥን በቀጣይ ጊዜያትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልጽግና ፓርቲ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዩ ትኩረት ስጥቶ እንደሚሠራ ሀላፊዋ ጠቁመው፤ አባላቱ ብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ምልክቱ የስንዴ ነዶ መሆኑን እንዲገነዘቡ አስተዋውቀዋል።

የኣሪ ዞን ሽግግር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ስመኝ ተስፋዬ፤ ሴቶ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ብሎም በሁሉ አቀፍ ዘርፍ ለውጥ እንዲያስመዘግቡ ፓርቲው ያከናወናቸው ተግባራት ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርተዋል ብለዋል።

በመሆኑም ሴቶች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሠላማዊና ተኣማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን እንወጣ ያሉት ወ/ሮ ስመኝ፤ ሴቶች በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የጂንካ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ደግፌ ጌታቸው ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊና አካባቢው ለውጥ እንዲመዘገብ መሪነቱን ተወጥቷል ብለው በዚህም ሴት እህቶቻችን ግንባር ቀደም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

የኣሪ ዞን ዋና አሰዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ ሀገራዊ ለውጡ በሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ከዳር እንዲደርስ እየተሠራ ነው ብለው ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ድርብ ሀላፊነት ያላቸው ሲሆን ይህንንም በብቃት መወጣት የሚችል አቅም አላቸው ብለዋል።

በቀጣይ ከለውጡ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ሴቶች በምርጫው ተሳትፎአቸውን እንዲያረጋግጡ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ አቅርበዋል።

የኣሪ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አፌዶ ወርቁ እንደ ሀገር ትላልቅ የሚታዩና የሚጨበጡ ለውጦች መመዝገባቸውን አብራርተው በዚህ ሂደት የሴቶች ተሳትፎ ጉልህ ነበር ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ የባህር በር ባለቤት መሆን እንድትችል ሴቶች ባላቸው አደረጃጀት ሠላማዊ ተሳትፎአቸውን እንዲያረጋግጡ አቶ አፌዶ ጠይቀው ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን እንዲውጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አለማየሁ ባውዲ፤ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ሀገራዊ ብልጽግናን ዕውን ማድረግ ነው ብለው ያለ ሴቶች ተሳትፎ የሚረጋገጥ ውጤት የለም ብለዋል።

ለፓርቲው ዕውቅና ለመስጠት የተገኙ ሴቶች 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በህዝቦች ተሳትፎ ያለምንም ችግር እንዲጠናቀቅ ሴቶች ድርብ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አቶ አለማየሁ ባውዲ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን