የአሊያንዝ አሬናው የነበልባል ምሽት

የአሊያንዝ አሬናው የነበልባል ምሽት

ዛሬ ምሽት እግር ኳስ ከጨዋታነት ባለፈ ወደ ጥበብ የሚቀየርበት፣ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የማጠቃለያ ምዕራፍ  ሙኒክ ላይ ይከናወናል።

ባለፈው ሳምንት በፓርክ ዴስ ፕሪንስ የታየው የዘጠኝ ግቦች የጎል ናዳ፣ ዛሬ በአሊያንዝ አሬና ለሚጠበቀው ፍልሚያ ትልቅ ማሟሟቂያ ነበር።

 በአንድ በኩል ለታሪክ እና ለክብር የሚፋለመው ባየር ሙኒክ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በሉዊስ ኤንሪኬ ጥበብ የታጀበውና የመጀመሪያውን ጨዋታ 5 ለ 4 በሆነ ውጤት መሪነቱን የጨበጠው ፒኤስጂ የቡዳፔስቱን የፍጻሜ ትኬት ለመቁረጥ ይፋለማሉ።

ባቫርያኑ ዛሬ ወደ ሜዳ የሚገቡት ከባድ የቤት ስራ ተጭኖባቸው ነው። በታሪካቸው በመጀመሪያው ጨዋታ ተሸንፈው ውጤት መቀልበስ የቻሉት ከ16 አጋጣሚዎች በ4ቱ ብቻ መሆኑ የስነ-ልቦና ጫና ሊፈጥርባቸው ቢችልም፣ ዛሬ ግን ከኋላቸው የሚጮኸው የሙኒክ ቀይ ባህር አለላቸው።

የዘንድሮው የሙኒክ የፊት መስመር እንደ ሰደድ እሳት የሚለበልብ ነው። ፒኤስጂ ደግሞ በዚህ ሜዳ ያለው ታሪክ ደካማ መሆኑ ለሀሪ ኬን እና ለጓደኞቹ ትልቅ የልብ ትርታ ሰጥቷቸዋል።

18 ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰው ይሄ የጀርመን ክለብ፣ 12ኛ የፍጻሜ ጉዞውን ለማረጋገጥ የአጥቂ መስመሩን ጦር አሳልቶ ይጠብቃል።

በፈረንሳዩ ክለብ በኩል ግን ሁኔታው የተለየ ነው። ስፔናዊው አሰልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ፣ ፒኤስጂን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሻምፒዮንስ ሊግ ባለቤት ካደረጉ በኋላ፣ አሁን ደግሞ በክብር መዝገብ ላይ ስማቸውን ከታላላቆቹ አንቸሎቲ እና ጋርዲዮላ ጎን ለማስፈር ቆርጠው ተነስተዋል።

 ዛሬ አሊያንዝ አሬና ላይ የሚኖራቸው 90 ደቂቃ ወይም ከዚያ በላይ የሚፈጅ ትግል፣ ለኤንሪኬ ሦስተኛውን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የማንሳት ህልም ድልድይ ነው።

እነዚህ ሁለት ግዙፍ ክለቦች እስካሁን ባደረጓቸው 17 ግንኙነቶች አንድም ጊዜ አቻ ተለያይተው አያውቁም!

 ይሄ ማለት ዛሬም በሙኒክ ምሽት አንድ ወገን በደስታ ሲፈነጥዝ ሌላኛው ደግሞ በሀዘን አንገቱን መድፋቱ የማይቀር መሆኑን ያሳያል።

ሆኖም የሁለቱም ቡድኖች ስብስብ በጉዳት ተፈትኗል። ሙኒክ እንደ ሰርጅ ግናብሪ እና ራፋኤል ጉሬሮ ያሉ ወሳኝ ተጫዋቹን ቢያጣም፣ ፒኤስጂም በመጀመሪያው ጨዋታ ድንቅ ብቃቱን ያሳየውን ተከላካይ አሽራፍ ሀኪሚን በጉዳት ማጣቱ የተከላካይ ክፍሉን ለከፍተኛ አደጋ ሊያጋልጠው ይችላል።

የአውሮፓ እግር ኳስ ማማ ላይ ለመውጣት፣ የአርሰናልን ተጋጣሚ ለመለየት እና ታሪክ ለመጻፍ ጥቂት ሰዓታት ቀርተዋል።

ባየር ሙኒክ የባቫርያዊያንን ወኔ ተጠቅሞ ውጤቱን ይቀለብሳል? ወይስ ፒኤስጂ የፓሪስን ልዕልና አጽንቶ ወደ ፍጻሜው ይጓዛል? ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ አሊያንዝ አሬና ምላሹን ይሰጠናል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ