በመንግስት ድጋፍና በህብረተሰቡ ተሣትፎ የተገነባው ጤና ጣቢያ በጎፋ ዞን ደንባ ጎፋ ወረዳ ወይዴ ውርኪ ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የተመረቀው ጤና ጣቢያው ከ20 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም ተመላክቷል።
ጤና ጣቢያው በህብረተሰቡ ተሣትፎና በመንግስት ድጋፍ የተገነባ መሆኑን የገለጹት የደንባ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ደበላ፤ የጤና ጣቢያው መገንባት የህዝቡ ዋነኛ ችግር ሆኖ የቆየውን የጤና ተግዳሮት የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና ጣቢያው ተመርቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የአካባቢው ነዋሪና የዞኑ አስተዳደር እንዲሁም ተቋማት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘላለም አበራ በበኩላቸው፤ መምሪያው ከጤና ጣቢያው ግንባታ ሂደት ክትትል አንስቶ ልዩ ልዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ፣ በምረቃው ዕለት የ1 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁሶችና የተሟላ የባለሙያ ቅጥር እንዲፈፀም መደረጉንም አብራርተዋል።
ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማስፋት ህብረተሰቡ ለጤናው መሠረተ ልማት የሚያደርገው ድጋፍ ከምንም በላይ ወሳኝነት እንዳለው ያነሱት አቶ ዘላለም፤ የተጀመረው ድጋፍ በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የዴንባ ጎፋ ወረዳ ወይዴ ውርኪ ማዕከል ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በጤና አገልግሎት እጦት ሳቢያ ይደርስባቸው የነበረውን እንግልትና የህይወት መስዋዕትነት የዞኑ አስተዳደር በመገንዘብ ለጤና ተቋሙ መገንባት በቁርጠኝነት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በጤና ጣቢያው መመረቅም የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ህብረተሠቡ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመደጋገፍ ለመስራት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
የዞኑ አስተዳደር ለጤና ተቋሙ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር በአካባቢው ለሚስተዋለው ከፍተኛ የመንገድ መሠረተ ልማትን ግንባታ እልባት እንዲያገኝ ከክልሉ መንግስት ጋር ተናበው እንደሚሠሩ ገልጸው ነዋሪዎችም የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
አስተያየታቸውን የሠጡን የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት በማዕከሉ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የጤና ተቋም ባለመኖሩ ለአገልግሎቱ ወደ አጎራባች ወረዳዎችና ዞኖች በሚያደርጉት ጉዞ ከፍተኛ መስዋዕትነት ሲከፍሉ መቆየታቸውን አብራርተዋል።
ዛሬ በአቅራቢያቸው የጤና ጣቢያው መገንባት ይህንን እንግልት የሚፈታላቸው መሆኑን በመጠቆም በቀጣይ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የሳውላ ማረሚያ ፖሊስ ተቋም ወንጀልን የሚጸየፉ አምራች ዜጎችን ለማፍራት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለፀ
በዳውሮ ዞን ገና ወረዳ የብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳና የፓርቲ ምርጫ ምልክት የማስተዋወቅ መርሃ ግብር ተካሄደ
ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የቡና ኮንፈረንስ ተጠናቋል