የአርሰናል የ20 ዓመታት የፍፃሜ ጥበቃ በቡዳፔስት ያበቃል!
ክቡራትና ክቡራን፤ በሰሜን ለንደን ሰማይ ስር ለሁለት አስርት ዓመታት የታመቀው ናፍቆት ዛሬ በደስታ እምባ ታጅቦ ፈንድቷል።
መድፈኞቹ ከ20 ዓመታት በኋላ፤ የአውሮፓን የእግር ኳስ ክብር ለመጎናጸፍ አንድ እርምጃ ብቻ ቀርቷቸዋል።
ትላንት ምሽት በኤምሬትስ ስታዲየም የታየው ትዕይንት ከጨዋታነት በላይ ነበር። አርሰናል የስፔኑን ግዙፍ አትሌቲኮ ማድሪድን አስተናግዶ፤ በመልሱ ጨዋታ በቡካዮ ሳካ ብቸኛ ጎል 1 ለ 0 በማሸነፍ፣ በድምር ውጤት 2 ለ 1 ለታሪካዊው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ መድረሱን አረጋግጧል።
ዴዬጎ ሲሞኒ የገነቡትን የመከላከያ ግንብ ሰብሮ ለመግባት መድፈኞቹ የታገሱት ትዕግስትና ያሳዩት ብስለት፣ የሻምፒዮንነት ግርማ ሞገስ የታየበት ነበር።
ከለንደን ሰፈር የተገኘው ድንቅ ኮከብ ቡካዮ ሳካ፣ አሁንም በታላላቅ መድረኮች ላይ የክለቡ ምልክት መሆኑን አስመስክሯል። በ45ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ያቺ ወርቃማ ጎል፣ አርሰናልን ወደ ቡዳፔስት አሻግራለች።
አሁን የቀረው አንድ ጥያቄ ብቻ ነው። በቡዳፔስት አርሰናልን የሚጠብቀው ማነው? ባየርን ሙኒክ ወይስ ፒኤስጂ? ማንኛውም ይሁን ማን፣ መድፈኞቹ ግን ከ20 ዓመት በኋላ ‘ታሪክ ራሱን ይደግማል ወይስ አዲስ ታሪክ ይጻፋል?’ የሚለውን ለመመለስ ዝግጁ ይመስላሉ።
ከ20 ዓመት በፊት በፓሪስ ያመለጣቸው ያ ዋንጫ፣ ዘንድሮ በቡዳፔስት እጃቸው ይገባ ይሆን? መላው የለንደን ቀይ ክፍል ምላሹን ለማግኘት በጉጉት እየጠበቀ ነው።
የአርሰናል የዘንድሮ የሻምፒዮንስ ሊግ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ወደ ቡዳፔስት የሚያደርሰው መንገድ በፈተናዎች የተሞላ፣ የተስፋ መቁረጥ ድመናዎች ያጠላሉትና የደጋፊዎችን ልብ በአጣብቂኝ ውስጥ የከተቱ ውጣ ውረዶች የታዩበት ነበር።
የዘንድሮው የቡዳፔስት ጉዞ በአንድ ጀምበር የተገኘ ስኬት አይደለም። አርሰናል ለዛሬው የታላቅነት ማማ ላይ ከመውጣቱ በፊት፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በእሳት ውስጥ አልፎ የተፈተነበትን ታሪክ ማስታወስ ይገባል።
ከሦስት ዓመት በፊት የነበረውን የ2022/23 የውድድር ዘመን እናስታውስ። መድፈኞቹ ለ248 ቀናት የሊጉን ሰንጠረዥ ቢመሩም፣ በመጨረሻዎቹ ሳምንታት በልምድ ማነስ ዋንጫውን ለማንቸስተር ሲቲ አሳልፈው ሰጡ። ያኔ ብዙዎች ‘አርሰናል እድሉን አባከነ’ ብለው ተሳለቁበት።
ነገር ግን ያ ሽንፈት ለዛሬው የአውሮፓ ስኬት ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነበር። ክለቡ በዚያ ዓመት ወደ ሻምፒዮንስ ሊግ መመለሱን በማረጋገጥ፣ ከስድስት ዓመታት የናፍቆት ርቀት በኋላ የአውሮፓን በር በታላቅ ግርማ አንኳኳ።
በ2023/24 የውድድር ዓመት ደግሞ አርሰናል ይበልጥ የተሟላ ቡድን ሆኖ ቀረበ። በሊጉ ለዋንጫ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ መፋለሙ ብቻ ሳይሆን፣ በሻምፒዮንስ ሊጉ እስከ ሩብ ፍፃሜ በመጓዝ ከባየርን ሙኒክ ጋር ያደረገው ፍልሚያ ቡድኑ በአውሮፓ መድረክ ከታላላቆቹ ጋር እኩል መቆም እንደሚችል ያስመሰከረበት ነበር።
በዚያው ዓመት በተለይ የተከላካይ ክፍሉ ጥንካሬ እና የቡድኑ የግብ መጠን፣ መድፈኞቹ ከ20 ዓመት በፊት የነበረውን ‘የማይበገሩት’ መንፈስ ዳግም እያነቃቁት መሆኑን አመላካች ነበር።
ባለፈው ዓመት በሻምፒዮንስ ሊጉ ለግማሽ ፍፃሜ ሲደርሱ ተጋጣሚያቸው የፈረንሳዩ ፒኤስጂ ነበር።
አርሰናል እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ተፋልሞ ለፍፃሜ ለመድረስ የነበረው ጥማት በዚያ ዓመት ታይቷል።
ያ የግማሽ ፍፃሜ ጉዞ ለዘንድሮው ቡድን ትልቅ ‘የልምድ ካፒታል’ ሆኖታል።
ያ ጉዞ ለአርሰናል ‘የመከፈቻ በር’ ነበር። ያኔ የግማሽ ፍፃሜውን ድባብ የለመዱት መድፈኞቹ፣ ዘንድሮ ያንን ልምድ ተጠቅመው አትሌቲኮን ጥለው ለፍፃሜ በቅተዋል። ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው ‘ጥረት’፣ ዛሬ ወደ ‘ውጤት’ ተቀይሮ መድፈኞቹን ወደ ቡዳፔስት አምርቷቸዋል።
ለዚህ ሁሉ ስኬት በዝውውር ገበያው ላይ የተደረጉ ጥበብ የተሞላባቸው ውሳኔዎች ትልቅ ድርሻ አላቸው። ከአራት ዓመታት በፊት ማርቲን ኦዴጋርድን በቋሚነት ማስፈረም፣ በመቀጠልም የዴክላን ራይስን መሰል ‘የመሀል ሜዳ ጄኔራል’ በአንድ መቶ ሚሊዮን ፓውንድ ማምጣቱ የቡድኑን የጀርባ አጥንት አጠናከረው። እነዚህ ዝውውሮች አርሰናል ‘ተሳታፊ’ ብቻ ሳይሆን ‘አሸናፊ’ ለመሆን የቆረጠ መሆኑን ለዓለም ያሳየባቸው ማስረጃዎች ነበሩ።
ባጭሩ፣ አርሰናል ዛሬ ለፍፃሜ የደረሰው ባለፉት ሦስት ዓመታት የሊጉን መሪነት ተቀምቶ፣ በጉዳት ታምሶና በውድቀት ተፈትኖ ያካበተው ‘የመሸነፍ ጥላቻ’ እና ‘የማሸነፍ ረሃብ’ ውጤት ነው። ዛሬ የምናየው ብስለት ትናንት በፈሰሰው እምባ እና ላብ የታነፀ ነው።
በአትሌቲኮ ማድሪድ ላይ የተመዘገበው ያ ድል፣ በነዚህ ሁሉ ውጣ ውረዶች ላይ የተቀመጠ የድል አክሊል ነው።
በጭንቅ ሰዓት ያልፈረሰው፣ በጉዳት ያልተንበረከከውና በትችት ያልተሸነፈው አርሰናል፣ ዛሬ ላይ የ20 ዓመታት ቆይታውን አክትሞ ለፍፃሜው ብቅ ብሏል።
ይህ ጉዞ የሚያስተምረን አንድ ነገር ቢኖር፦ ‘ትልልቅ ድሎች የሚመጡት በትልልቅ ፈተናዎች ውስጥ ካለፉ በኋላ ነው’ የሚለውን እውነት ነው።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
አርሰናል ከ20 ዓመታት በኋላ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለፍፃሜ ደረሰ
አርባምንጭ ከተማ መቀሌ 70 እንደርታን አሸነፈ
“ከማንችስተር ዩናይትድ ልወጣ እችል ነበር፤ ነገር ግን እዚህ ስኬታማ መሆን ትልቅ ትርጉም አለው”ብሩኖ ፈርናንዴዝ