የጎፋ ዞን ልማት ማህበር ሥራ አመራር ቦርድ የ3ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ አካሄደ
የማህበሩ ሥራ አመራር ቦርድ የ2018 ዓ.ም አፈጻጸም ግምገማ እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በሣውላ ከተማ አካሂዷል።
የጎፋ ዞን ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ዮናታን ጀረኔ የጎፋ ዞን ልማት ማህበር የሁሉም ህዝብ ተቋም በመሆኑ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ሀብት በማመንጨት ከህብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረጉን ጠቁመዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የወላይታ ሶዶ ክላስተር አስተባባሪ እና የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊና የቦርዱ አባል አቶ ተፈሪ አባተ በበኩላቸው፥ በልማት ማህበሩ በዘጠኝ ወራት የተከናወኑትን መገምገማቸውንና በቀጣይ 75 ቀናት በሚከናወኑ ተግባራት ዙርያ ቦርዱ መምከሩን ተናግረዋል።
አክለውም የልማት ማህበሩ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር በአከባቢው ተፈጥሮ የለገሰውን ፀጋ አሟጦ በመጠቀም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ፥ ልማት ማህበሩ በዞኑ የሚገኘውን የሉጸ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመደገፍ ውጤታማ ማድረጉን ገልጸው፥ በተፈጥሮ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉን እና በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች የማህበረሰብ አቀፍ የመድኃኒት መሸጫ መደብሮችን በማስገንባት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ለአብነት በመጥቀስ አፈጻጸሙን አድንቀዋል።
የጎፋ ዞን ልማት ማህበር ስራ አስክያጅ ኢንጃነር ነጻነት ገመዳ ልማት ማህበሩ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፈሎች በማደራጀት ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናገረው፥ ማህበረሰቡ በበጎ ፈቃድ ማህበሩን ለመደገፍ አባል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ማህበሩ በሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ስለመሆኑ በውይይት መድረኩ ላይ አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ባህላዊ እሴትና የወንድማማችነት ትስስርን የሚያድስ የ“ኦዴ ኦሶ” ቤተሰብ ምረቃ ስነ-ስርዓት በልዩ ድምቀት ተካሄደ
የሀይማኖት ተቋማት በመተባበር እና በመነጋገር ለሀገር ግንባታ በጋራ ልንሰራ ይገባል – የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ
የምሁራን አንድነትን ማጠናከርና የእርስ በእርስ መከባበር ባህልን ማጎልበት ለአካባቢው ዘላቂ ሠላም መስፈን ወሳኝነት እንዳለው ተመላከተ