አሽሊ ያንግ ጫማውን ሰቀለ

አሽሊ ያንግ ጫማውን ሰቀለ

በእንግሊዝ እግር ኳስ ውስጥ በጽናቱ እና በሁለገብ ተጫዋችነቱ የሚታወቀው አንጋፋው የመስመር ተጫዋች አሽሊ ያንግ፣ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ የዘለቀውን ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወቱን በይፋ ማክተሙን አስታውቋል።

ያንግ በሜዳ ላይ በነበረው ቆይታ እጅግ አስደናቂ የሚባሉ ቁጥሮችን ማስመዝገብ ችሏል።

 በተለይም በዓለም ላይ በጠንካራነቱ በሚታወቀው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ 485 ጨዋታዎችን በማድረግ በሊጉ ታሪክ የማይረሳ አሻራውን አሳርፏል።

 በተጨማሪም የአገሩን የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድንን መለያ ለብሶ 39 ጊዜ ወደ ሜዳ መግባት ችሏል።

አሽሊ ያንግ በሄደበት ክለብ ሁሉ ለስኬት ቅርብ የነበረ ተጫዋች ነው።

 በካቢኔው ውስጥ ካስቀመጣቸው ትልልቅ ድሎች መካከል፦1 የኢንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ እና 1 የጣልያን ሴሪ አ ዋንጫን በማንሳት በሁለት የተለያዩ አገራት የሊግ ሻምፒዮን መሆን ችሏል።

በተጨማሪም 1 የዩሮፓ ሊግ፣1 የኤፍ ኤ ካፕ ፣ 1 የሊግ ካፕ እና 2 የኮሚኒቲ ሺልድ ድሎችን አጣጥሟል።

ከዋትፎርድ ተነስቶ በአስቶን ቪላ ደምቆ፣ በማንቸስተር ዩናይትድ የክብር ማማ ላይ የወጣው ያንግ፤ በኋላም በኢንተር ሚላን እና ኤቨርተን ባሳየው ብቃት ዘመናዊ እግር ኳስ የሚጠይቀውን ተለዋዋጭነት በተግባር አሳይቷል።

 ከአጥቂ መስመር ተጫዋችነት ወደ መስመር ተከላካይነት በመቀየር እስከ 38 ዓመቱ ድረስ በከፍተኛ ደረጃ መጫወት መቻሉ ለብዙዎች አርአያ ያደርገዋል።

የአሽሊ ያንግ 23 ዓመታት የእግር ኳስ ህይወት ዛሬ ላይ ቢጠናቀቅም፣ ስሙ ግን በፕሪሚየር ሊጉ የታሪክ መዝገብ ላይ በደመቀ ቀለም ተጽፎ ይኖራል።

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ