ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ሳንድሮ ቶናሊን ለማስፈረም ፉክክር ጀምረዋል
ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 23/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በመጪው የክረምት የዝውውር መስኮት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ታላላቅ ክለቦች ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል የኒውካስል ዩናይትዱን አማካይ ሳንድሮ ቶናሊን ለማስፈረም ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየታቸው ተሰምቷል።
እንደ “ዘ ሰን” ዘገባ ከሆነ፥ ሁለቱ ክለቦች የቀድሞውን የኤሲ ሚላን ኮከብ ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ዝግጁ ናቸው።
ኒውካስል ዩናይትድ በበኩሉ የፋይናንስ ሚዛኑን ለመጠበቅ አንዳንድ ቁልፍ ተጫዋቾቹን ለመሸጥ እንደሚገደድ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ቶናሊም ከሚሸጡት ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ቀዳሚው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ስለ ዝውውሩ መረጃዎችን በማቀበል የሚታወቀው ፋብሪዚዮ ሮማኖ እንደገለጸው፥ ጣሊያናዊው አማካይ ወደ ሀገሩ ጣሊያን (ሴሪ አ) የመመለስ ፍላጎት የለውም። ይልቁንም ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ላይ ለመቆየት አድርጓል።
ይህ መረጃ ቶናሊን በቅርበት ለሚከታተሉት ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ትልቅ ተስፋን ሰጥቷል።
ኒውካስል ተጫዋቹን በ2023 ከኤሲ ሚላን ሲያስፈርመው 55 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ ማድረጉ ይታወሳል።
አሁን ላይ ክለቡ ለተጫዋቹ የጠየቀው ዋጋ በእጥፍ አድጎ 110 ሚሊዮን ፓውንድ አካባቢ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ኒውካስል በአሁኑ ወቅት በደረጃ ሰንጠረዡ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ ሊጉ ሊጠናቀቅ አራት ጨዋታዎች እየቀሩት በሂሳብ ስሌት ገና ከወራጅ ቀጠናው ሙሉ በሙሉ ነፃ አልሆነም።
ማንችስተር ዩናይትድ አማካይ ክፍሉን ለማጠናከር እና አዲስ የፈጠራ ብቃት ያለው ተጫዋች ለመጨመር ቶናሊን እንደ ተመራጭ እያዩት ይገኛሉ።
በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመራው አርሰናልምዐበመሀል ሜዳ ላይ ያለውን ጥልቀት ለመጨመር እና የቴክኒክ ብቃቱ ከፍተኛ የሆነ ተጫዋች ለማግኘት ቶናሊን ወደ ኤምሬትስ ማምጣት ይፈልጋል።
በቀጣዮቹ ሳምንታት የኒውካስል በሊጉ የመቆየት እድል እና የክለቦቹ ድርድር የቶናሊን የወደፊት ቆይታ በይፋ የሚወስን ይሆናል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
አሽሊ ያንግ ጫማውን ሰቀለ
“በቀጣይ የውድድር ዘመን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት እንችላለን” — ሜሰን ማውንት
ከሚያዝያ 22 ጀምሮ በጂንካ ከተማ ለሚስተናገደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና የመጨረሻ የዝግጅት ምዕራፍ ግምገማ መካሄዱን የክልሉ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከስታወቀ