“በቀጣይ የውድድር ዘመን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት እንችላለን” — ሜሰን ማውንት

“በቀጣይ የውድድር ዘመን የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት እንችላለን” — ሜሰን ማውንት

የማንቸስተር ዩናይትዱ አማካይ ሜሰን ማውንት ክለቡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን የኢንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን የማሸነፍ ብቃትና ስነ-ልቦና እንዳለው በልበ ሙሉነት ተናግሯል።

ዩናይትድ የሊጉን ዋንጫ ለመጨረሻ ጊዜ ካነሳ 13 አመታት ቢቆጠሩም፣ ማውንት ግን ይህ የታሪክ ድርቅ የሚያበቃበት ጊዜ ሩቅ እንዳልሆነ ያምናል።

ከቼልሲ በ55 ሚሊዮን ፓውንድ ዝውውር ኦልድትራፎርድ የደረሰው የ27 አመቱ አማካይ፣ ለክለቡ እስካሁን 69 ጨዋታዎችን አድርጓል።

 ማውንት ስለ ቀጣዩ አላማው ሲናገር”ከዚህ ቀደም የሻምፒዮንስ ሊግን ዋንጫ አሳክቻለሁ፤ አሁን ደግሞ የፕሪምየር ሊግ ባለቤት የመሆን ትልቅ ህልም አለኝ። ይህንን ማድረግ እንችላለን? አዎ፣ አምናለሁ!” ብሏል።

ማውንት አክሎም “ምናልባት አሁን ላይ ነገሩ ትንሽ ራቅ ያለ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን እንደ ቡድን ራስን ለማብቃት የግድ እንዲህ አይነት ጠንካራ ስነ-ልቦና ሊኖርህ ይገባል። እንደ ማንቸስተር ሲቲ፣ ሊቨርፑል፣ ቼልሲ እና አርሰናል ባሉ ትላልቅ ክለቦች ላይ ምን ማድረግ እንደምንችል በተግባር አሳይተናል። አሁን የቀረን ነገር ቢኖር ይሄንን ጥንካሬ በቋሚነት ማስቀጠል ነው” ሲል ገልጿል።

ምንም እንኳን ማውንት በዚህ የውድድር ዘመን ካደረጋቸው 20 የሊግ ጨዋታዎች መካከል በቋሚነት የጀመረው በ10ሩ ብቻ ቢሆንም፣ በክለቡ ያለው ተስፋ ግን አልደበዘዘም።

 በተለይም በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ስር ያለው ሚና ላይ ጥያቄዎች ቢነሱም፣ ካሪክ ተጫዋቹን ማድነቃቸውን አልተዉም።

ማውንት በተደጋጋሚ በሚያጋጥሙት ጥቃቅን ጉዳቶች ምክንያት ከቶማስ ቱሄል የኢንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ጥሪ ቢርቅም፣ በራሱ እንደሚተማመን ግን አልሸሸገም።

 “ሁልጊዜም ቢሆን በራሴ እተማመናለሁ። ለዚህ ታላቅ ክለብ ምን ማበርከት እንደምችል አውቃለሁ። ዩናይትድን ወደነበረበት የክብር ማማ ለመመለስ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የድርሻዬን መወጣት ለእኔ ልዩ ትርጉም አለው” ብሏል።

ሜሰን ማውንት ይህንን አስተያየት የሰጠው በገንዘቡ ድጋፍ ባደረገለት ‘ሜክ ኤ ዊሽ’  ፋውንዴሽን ዝግጅት ላይ ተገኝቶ በነበረበት ወቅት ነው።

 ወደፊትም በሙሉ ጊዜ አሰልጣኝነት የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው በዚሁ አጋጣሚ ፍንጭ ሰጥቷል።

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ