የማንቸስተር ሲቲ ጥያቄ ውድቅ ተደረገ
ማንችስተር ሲቲ ሁለት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች የመጫወቻ ጊዜ ሰሌዳ እንዲቀየርለት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎበታል።
ማንቸስተር ሲቲ በኤፍኤ ካፕ ለፍጻሜ ማለፉን ተከትሎ፣ በሊጉ የነበሩት የክሪስታል ፓላስ እና የቦርንማውዝ ጨዋታዎች እንዲራዘሙ መደረጋቸው ይታወሳል።
ክለቡ በጨዋታዎች መካከል በቂ የማገገሚያ ጊዜ ለማግኘት የሁለቱን ጨዋታዎች ቅደም ተከተል ለመቀየር ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ የፕሪምየር ሊጉ የበላይ አካል ግን ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ የቀድሞው መርሃ ግብር እንዲቀጥል ወስኗል።
በሊጉ ውሳኔ መሠረት ማንቸስተር ሲቲ በሰባት ቀናት ውስጥ ሶስት ወሳኝ ጨዋታዎችን ያከናውናል።
ረቡዕ፣ ግንቦት 5 ከክሪስታል ፓላስ ጋር በኢቲሃድ ስታዲየም፣ቅዳሜ፣ ግንቦት 8 የኤፍኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ከቼልሲ ጋር በዌምብሌይ ስታዲየም እንዲሁም ማክሰኞ፣ግንቦት 11 ከቦርንማውዝ ጋር ከሜዳ ውጭ በቪታሊቲ ስታዲየም የሚጫወት ይሆናል።
ይህ ውሳኔ በተለይ ከአርሰናል ጋር ለዋንጫ ብርቱ ፉክክር እያደረገ ለሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ትልቅ ራስ ምታት ሆኗል።
ፔፕ ጋርዲዮላ በ7 ቀናት ውስጥ ሶስት ወሳኝ ጨዋታዎችን ማድረጉ በተጫዋቾቹ ላይ የአካል ብቃት ድካም ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ቢገልጹም፣ ሊጉ ግን ለሌሎች ክለቦች እና ለቴሌቪዥን ስርጭት መርሃ ግብሮች ሲባል ለውጥ አላደረገም።
በተለይ ከኤፍኤ ካፕ ፍጻሜ ሶስት ቀናት በፊት እና ከሶስት ቀናት በኋላ የሊግ ጨዋታዎችን ማድረጉ ሲቲ ያለውን ጥልቅ ስብስብ በአግባቡ እንዲጠቀም ያስገድደዋል።
ከነዚህ ጨዋታዎች በኋላ በሊጉ መዝጊያ ሳምንት ማንቸስተር ሲቲ አስቶን ቪላን በሜዳው ያስተናግዳል።
የሊጉ ውሳኔ ለማንቸስተር ሲቲ “ፈተና” ለአርሰናል ደግሞ “መልካም አጋጣሚ” ሊሆን እንደሚችል የ እየተገለፀ ይገኛል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ካይ ሀቨርትዝ ከጉዳቱ በቶሎ የማገገም ተስፋ አለው
“በአሞሪም ጊዜ ሽንፈት ይከተለን ነበር፤ አሁን ግን ተለውጠናል!” – ሀሪ ማጓየር
የፕሪሚየር ሊጉ የሳምንቱ መሳጭ ፍልሚያዎች፡ አርሰናል መሪነቱን ለማስመለስ፣ ሊቨርፑል ለሦስተኛ ተከታታይ ድል!