“በአሞሪም ጊዜ ሽንፈት ይከተለን ነበር፤ አሁን ግን ተለውጠናል!” – ሀሪ ማጓየር
የማንችስተር ዩናይትዱ ተከላካይ ሃሪ ማጓየር ቡድኑ በሚካኤል ካሪክ ስር እያሳየ ስላለው መሻሻል የሰጠው አስተያየት በኦልድ ትራፎርድ አዲስ ንፋስ መነፈሱን አመላካች ሆኗል። ተጫዋቹ የቀድሞው አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በነበሩበት ወቅት ቡድኑ ለውጤት ይቸገር እንደነበር በግልጽ ተናግሯል።
ማጓየር እንደገለጸው፤ በአሞሪም ስር ዩናይትድ ጨዋታዎችን በእኩልነት ቢጀምርም መጨረሻው ግን የሽንፈት ነበር። “ውጤቱ ራሱ ይናገራል” ያለው ማጓየር፣ ካሪክ ከመጣ በኋላ የተደረገው የቅርጽ ለውጥ ቡድኑን ወደ ውጤታማነት እንደመለሰው ገልጿል።
“አሞሪም እዚህ በነበሩበት ወቅት ጨዋታዎች ሃምሳ በሃምሳ (50/50) ነበሩ፤ ነገር ግን መጨረሻችን ሁልጊዜም ሽንፈት ነበር።” ሀሪ ማጓየር ተናግሯል።
ማጓየር ለውጡ የመጣው ቡድኑ በሁለቱም የሜዳ ክፍሎች ላይ ባሳየው ጥንካሬ እንደሆነ ያምናል።
በተከላካይ ክፍል በኩል ቡድኑ ግብ እንዳይቆጠርበት ያለው ጥንካሬ መጨመሩን እንዲሁም በማጥቃቱ ደግሞ የሚገኙ አጋጣሚዎችን ወደ ግብ የመቀየር ብቃት መሻሻሉን ጠቁሟል።
የማጓየር ንግግር በደጋፊዎች ዘንድ ሁለት አይነት ስሜትን ፈጥሯል።
አንዳንዶች “ተጫዋቾቹ ለአሞሪም አልተጫወቱም ነበር?” የሚል ጥያቄ ሲያነሱ፣ አብዛኞቹ ግን የካሪክን የታክቲክ ብስለትና ቡድኑን የማረጋጋት ብቃት እያደነቁ ይገኛሉ።
ዩናይትድ በዚህ ግስጋሴው ከቀጠለ፣ ካሪክ ከጊዜያዊ አሰልጣኝነት ባለፈ የክለቡን የረጅም ጊዜ አቅጣጫ ሊቀይር እንደሚችል እየተነገረ ነው።
ማንቸስተር ዩናይትድ የውድድር ዘመኑ ሊጠናቀቅ 4 ጨዋታዎች እየቀሩት በፕሪምየር ሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ 3ኛ ላይ ተቀምጧል።
የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን በሂሳባዊ ስሌት ለማረጋገጥ አሁን የሚያስፈልገው 1 ነጥብ ብቻ ነው።
የማጓየር ምስክርነት ለካሪክ ትልቅ የልብ መተማመኛ ሲሆን፣ ለሩበን አሞሪም አድናቂዎች ደግሞ መርዶ ሆኖባቸዋል።
የሃሪ ማጓየር አስተያየት ቡድኑ በአሰልጣኞች ለውጥ ውስጥ እያለፈ ያለውን የውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያሳይ ቢሆንም ይህ መሻሻል ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የቡድን ግንባታ መሰረት ይሆን ወይንስ ለጊዜው የተገኘ ስኬት ብቻ ነው ብለው ያስባሉ?
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የፕሪሚየር ሊጉ የሳምንቱ መሳጭ ፍልሚያዎች፡ አርሰናል መሪነቱን ለማስመለስ፣ ሊቨርፑል ለሦስተኛ ተከታታይ ድል!
ማኑኤል ኖየር፣ በባየር ሙኒክ እስከ 2027 ለመቆየት ተስማማ
“ቡካዮ ሳካ እና ሪካርዶ ካላፊዮሪ ለኒውካስል ጨዋታ ወደ ቡድኑ የመመለስ ‘እድል’ አላቸው” – ሚኬል አርቴታ