የፕሪሚየር ሊጉ የሳምንቱ መሳጭ ፍልሚያዎች፡ አርሰናል መሪነቱን ለማስመለስ፣ ሊቨርፑል ለሦስተኛ ተከታታይ ድል!

የፕሪሚየር ሊጉ የሳምንቱ መሳጭ ፍልሚያዎች፡ አርሰናል መሪነቱን ለማስመለስ፣ ሊቨርፑል ለሦስተኛ ተከታታይ ድል!

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 34ኛ ሳምንት መርሐ ግብር የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ ግጥሚያዎች ዛሬም ብርቱ ፉክክር ይስተናገድባቸዋል።

መሪነቱን ለማንቼስተር ሲቲ ያስረከበው አርሰናል እንዲሁም የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የሚጋደሉት አስቶንቪላ እና ሊቨርፑል ተጠባቂ ጨዋታዎቻቸውን ያደርጋሉ።

የአርሰናል እና ኒውካስል ፍልሚያ፡ የደረጃ ስጋት ወይስ የአሸናፊነት ጉዞ?

ባለፉት ሦስት የውድድር ዓመታት በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወሰው አርሰናል፤ ዘንድሮም ያ ታሪክ እንዳይደገም በደጋፊዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ነግሷል።

ከካራባኦ ካፕ እና ከኤፍ ኤ ዋንጫ ውጪ የሆነው የሰሜን ለንደኑ ክለብ፤ አሁን ትኩረቱን በቀሪዎቹ ሁለት ውድድሮች ላይ አድርጓል።

በሊጉ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው አርሰናል፤ ወደ ድል ለመመለስ ቆርጦ ተነስቷል። ለዚህም የቡካዮ ሳካ እና የሪካርዶ ካላፊዮሪ ወደ ስብስብ መመለስ ለሚኬል አርቴታ ትልቅ ግብዓት ሆኗል።

ተጋጣሚው ኒውካስልም ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት የደረሰበት በመሆኑ ዛሬ በኢምሬትስ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፉት 5 ግንኙነቶች አርሰናል 3 ጊዜ ሲያሸንፍ፤ ኒውካስል በ2ቱ ድል ቀንቶታል።

ጨዋታው ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል።

ሊቨርፑል ከክሪስታል ፓላስ፡ የአንፊልድ የበቀል ጉዞ?

በሊጉ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማሳካት የሚጋጠመው ሊቨርፑል፤ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ ዕድሉን ለማጥበቅ ወደ ሜዳ ይገባል።

የሚገርመው ሊቨርፑል በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ያሳየውን ግስጋሴ ገትቶ የመጀመሪያውን ሽንፈት ያስቀመሰው ክሪስታል ፓላስ መሆኑ ነው።

ባለፉት 5 የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ፓላስ 2 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው፤ ሊቨርፑል ያሸነፈው 1 ጊዜ ብቻ ነው።

ቀሪዎቹ 2 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

የሁለቱ ክለቦች ተጠባቂ ፍልሚያ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በአንፊልድ የሚካሄድ ይሆናል።

ፉልሃም ከአስቶንቪላ፡ የኡናይ ኢምሬ የድል ግስጋሴ

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የሚፋለመው አስቶንቪላ፤ በክራቨን ኮቴጅ እንግዳ ይሆናል።

በኡናይ ኢምሬ የሚመራው ቪላ፤ ባለፉት 5 የእርስ በእርስ ጨዋታዎች ፉልሃምን ሙሉ በሙሉ (5 ጊዜም) በማሸነፍ ፍጹም የበላይነት አለው።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ያላደረገው ፉልሃም፤ በሜዳውና በደጋፊው ፊት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል።

ይህ ጨዋታ ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ሲል ይካሄዳል።

11 ሰዓት ላይ በሚካሄዱ ሌሎች መርሐ ግብሮች መውረዱን ያረጋገጠው ዎልቭስ ከሰሜን ለንደኑ ቶተንሃም ጋር ይፋለማል።

ላለመውረድ የሚፋለመው ዌስትሃም ዩናይትድ ደግሞ በሜዳው ኤቨርተንን ይጋብዛል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ