“ቡካዮ ሳካ እና ሪካርዶ ካላፊዮሪ ለኒውካስል ጨዋታ ወደ ቡድኑ የመመለስ ‘እድል’ አላቸው” – ሚኬል አርቴታ
ሁለቱ የአርሰናል ተጫዋቾች ቡካዮ ሳካ እና ሪካርዶ ካላፊዮሪ ክለባቸው በነገው ዕለት ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የመሰለፍ ዕድል እንዳላቸው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ተናግረዋል።
አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ እንደገለጹት፤ ቡካዮ ሳካ እና ሪካርዶ ካላፊዮሪ አርሰናል ከኒውካስል ዩናይትድ ጋር ለሚያደርገው የፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ “ምናልባትም በስብስቡ ውስጥ ይካተታሉ።”
የ24 ዓመቱ ቡካዮ ሳካ በመጋቢት ወር አርሰናል በካራባኦ ካፕ ፍፃሜ በማንቸስተር ሲቲ ከተሸነፈበት ጨዋታ በፊት በነበረው ከሀገራት የጨዋታ ሰሞን ጀምሮ ጉዳት ላይ ቆይቷል።
ምንም እንኳን ለቶማስ ቱከል የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ተጠርቶ የነበረ ቢሆንም እንደ ዲክላን ራይስ ልምምድ ሳይሰራ ወደ አርሰናል ተመልሷል።
የ23 ዓመቱ ሪካርዶ ካላፊዮሪ መጨረሻ ላይ የተጫወተው በሻምፒዮንስ ሊግ ከስፖርቲንግ ጋር በነበረው ጨዋታ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን በደረሰበት መጠነኛ ጉዳት ሶስት ጨዋታዎችን አምልጦታል።
ኔዘርላንዳዊው ተከላካይ ዩሪየን ቲምበር ግን ለኒውካስሉ ጨዋታ በስብስቡ ውስጥ እንደማይካተት ተረጋግጧል።
አርቴታ ስለ ሳካ እና ካላፊዮሪ ሲናገሩ “አሁን ከእነሱ ምርጥ ብቃታቸውን ማውጣት ይኖርብናል። ዝግጁ መሆን ብቻ በቂ አይደለም፤ በዚህ የውድድር ዘመን ወቅት የሚያስፈልገን በምርጥ ብቃታቸው ላይ ሆነው መገኘታቸው ነው። ነገር ግን ቢያንስ ከእኛ ጋር መሆናቸው በራሱ ጥንካሬ ይፈጥርልናል።” ሲሉ ተደምጠዋል።
አርቴታ አክለውም “ሳካ ብቃቱን ለማስቀጠል የሚቸገርበት ወቅት ነበር፤ ምክንያቱም ጨርሶ ምቾት አይሰማውም ነበር። አሁን ግን ተገቢውን ህክምና እና እረፍት አግኝቷል። አሁን የውድድር ዘመኑ ወሳኝ ወቅት ነው፣ እሱም ወደ እኛ ተመልሷል።” በማለት ገልጸዋል።
አርሰናል ነገ ቅዳሜ ከምሽቱ 1 ሰዓት 30 በሜዳው ኒውካስልን ይገጥማል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ማኑኤል ኖየር፣ በባየር ሙኒክ እስከ 2027 ለመቆየት ተስማማ
“እዚህ መሆን ደስ ይለኛል!” – ማይክል ካሪክ
ማቲያስ ዴሊኽት ወደ ሜዳ ለመመለስ ልምምድ ጀመረ