“እዚህ መሆን ደስ ይለኛል!” – ማይክል ካሪክ
በማንቸስተር ዩናይትድ ቤት በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ድንቅ ስራ እየሰራ የሚገኘው የቀድሞው የክለቡ አማካይ ማይክል ካሪክ፤ ክለቡን በቋሚነት ስለመምራት ለቀረበለት ጥያቄ ግልጽ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።
ይሁን እንጂ በክለቡ ያለውን ቆይታ በእጅጉ እየተገበረው መሆኑን በኩራት ገልጿል።
ማይክል ካሪክ ከብሬንትፎርድ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለ ቋሚ ቅጥር የቀረበለትን ጥያቄ ሲመልስ “እዚህ መሆን እወዳለሁ፤ አሁን ባለሁበት ሃላፊነትም ደስተኛ ነኝ። እስካሁን ጥሩ ውጤቶችን አስመዝግበናል፣ አቋማችንም በርታ ያለ ነው። ሆኖም ገና ብዙ የሚቀሩ ስራዎች አሉ፤ የቡድኑን ደረጃ ከዚህ በላይ ከፍ ማድረግ እንፈልጋለን።” ብሏል።
ካሪክ አክሎም በክለቡ እስከቆየበት ጊዜ ድረስ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጾ፤ የውሳኔው ባለቤት ግን እርሱ እንዳልሆነ አመልክቷል።
ማይክል ካሪክ ከጥር ወር ጀምሮ ቡድኑን ከተረከበ በኋላ ማንቸስተር ዩናይትድ በሊጉ ካሉ ክለቦች በሙሉ ብልጫ ያለው ነጥብ በመሰብሰብ ላይ ይገኛል።
ካለፉት 12 ጨዋታዎች 8ቱን ማሸነፍ ችሏል።
ዩናይትድን ወደ 3ኛ ደረጃ በማውጣት የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን ለማረጋገጥ ተቃርቧል።
በሩበን አሞሪም ዘመን የነበረውን አለመረጋጋት በመቀየር በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን አግኝቷል።
የክለቡ ባለቤት ሰር ጂም ራትክሊፍ ካሪክ ድንቅ ስራ እየሰራ መሆኑን ቢያምኑም ስለ ቋሚ ቅጥሩ ግን “ያልደረስንበት ጉዳይ ነው” በሚል ዝምታን መርጠዋል።
ክለቡ እስከ ሚያዝያ ወር መጨረሻ ወይም ግንቦት መጀመሪያ ድረስ የቋሚ አሰልጣኝ ቅጥር ሂደቱን ለመቋጨት እቅድ እንዳለው ይነገራል።
የቀድሞ የቡድን አጋሮቹ ጋሪ ኔቪል እና ዌይን ሩኒ በካሪክ ስራ ቢደሰቱም ክለቡ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት በጥንቃቄ ማሰብ እንዳለበት ያስጠነቅቃሉ።
ሆኖም እንደ ፓትሪስ ኤቭራ እና ራያን ጊግስ ያሉ አንጋፋዎች ካሪክ ለቦታው ብቁ መሆኑን በመግለጽ ድጋፋቸውን እየቸሩት ይገኛሉ።
ካሪክ በጊዜያዊነት የጀመረውን ጉዞ በቋሚነት “የኦልድ ትራፎርድ ንጉስ” በመሆን ያጠናቅቀው ይሆን? የውድድር ዘመኑ ማብቂያ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ማቲያስ ዴሊኽት ወደ ሜዳ ለመመለስ ልምምድ ጀመረ
የደም ትስስር በሜዳ ላይ
ሲዳማ ቡና መቀሌ 70 እንደርታን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናከረ