ከመማር ማስተማር ተግባር ባለፈ የአካባቢ ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የሚዛን ግብርና ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ አስታወቀ

ከመማር ማስተማር ተግባር ባለፈ የአካባቢ ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የሚዛን ግብርና ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ አስታወቀ

ኮሌጁ ከፊታችን የሚከበረውን የፋሲካ በአል ምክንያት በማድረግ አስራ አምስት ሺ እንቁላል እና አንድ ሺ አምስት መቶ የስጋ ዶሮዎችን በሰንበት ገበያ ለህብረተሰቡ ማቅረቡን አስታውቋል።

በ1994 ዓ.ም እንደተመሰረተ የሚነገርለት የዛሬው የሚዛን ግብርና ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የግብርና ባለሙያዎችን በማሰልጠን እና በማፍራት ወደአርሶአደሩ በማስገባት የአርሶአደሩን ተግባር በማገዝ በኩል ብዙ ተግባራትን ማከናወኑን ነው የኮሌጁ የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዲን ግርማ ለገሰ የተናገሩት።

እንዲሁም የተሻሻሉ የተለያዩ ዝርያ ብዜቶችን ወደ ማህበረሰብ በማሰራጨት በኩል ኮሌጁ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደሀገር በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም ኮሌጁ በራሱ ገቢ መተዳደር እንዳለበት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በኢንተርፕራይዞች አማካይነት ሰርቶ ማሳያ በማዘጋጀት በተሰራው ስራ ተቋሙ የአመት ገቢውን ከአራት ሚሊየን ወደ ሰላሳ ስድስት ሚሊየን ብር ማሳደግ ችሏል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም የአካባቢውን ገበያ በማረጋጋት በኩል በተለይም በዶሮ ርባታ ዘርፍ ከፊታችን ለሚከበረው የፋሲካ በአል 1 ሺ 5 መቶ ዶሮዎችን እና አስራ አምስት ሺ እንቁላሎችን ለሰንበት ገበያ ማቅረብ መቻላቸውን ተናግረዋል።

ከኮሌጁ መምህራን መካከልም መምህር ከድር አብደላ እና መምህር ሙርቴሳ ለገሰ የእርባታ ትምህርት ክፍል መምህራን ሲሆኑ በኮሌጁ ከሚሰጠው ተግባር ተኮር ትምህርት ባለፈ ለህብረተሰቡ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ እንዲሁም የኮሌጁን ገቢ በማሳደግ በኩል እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም በኮሌጁ የዶሮ እርባታ ከተጀመረ በኋላ ሰባት ሺ የአንድ ቀን የእንቁላል ጣይ ጫጬቶችን በማስገባት በቀን በአማካይ ከአምስት ሺ በላይ እንቁላሎችን ማግኘት መቻላቸውን ጠቁመው፤ እንቁላሉንም ለአካባቢው ማህበረሰብ በማቅረብ የገበያ ማረጋጋት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።

ለአከባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል መፈጠሩንም ነው የተናገሩት።

በኮሌጁ የዶሮ እርባታው ጣቢያ ላይ የስራ እድል የተፈጠረላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ከዚህ ቀደም ስራ ያልነበራቸው እንደነበር እና በአሁኑ ሰአት በኮሌጁ የስራ እድል ተመቻችቶላቸው ተጠቃሚ እንደሆኑም ገልጸዋል።

ወደፊትም ባገኙት እውቀት የራሳቸውን የዶሮ ርባታ ለመጀመር ማቀዳቸውን ጠቁመዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን