ማህበራዊ ሚዲያ ጊዜና ቦታ ሳይገድበው መረጃን በፍጥነት ተደራሽ ስለሚያደርግ ተጠቃሚዎች ትክክለኛ እና ተአማኒነት ያለውን መረጃ ማሰራጨት ይጠበቅባቸዋል – ዶ/ር በኃይሉ ገ/ማሪያም
ማህበራዊ ሚዲያ ጊዜና ቦታ ሳይገድበው መረጃን በፍጥነት ተደራሽ ስለሚያደርግ ተጠቃሚዎች ትክክለኛ እና ተአማኒነት ያለውን መረጃ ማሰራጨት እንደሚጠበቅባቸው በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሮኒክስ ለርኒንግ ዳይሬክተር ዶ/ር በኃይሉ ገ/ማሪያም ገለጹ፡፡
የኤሌክትሮኒክስ ለርኒንግ ኢንሼቲቭ በትምህርት ሚኒስቴር ጸድቆ ወደሥራ ከገባ አንድ ዓመት መሆኑን የገለጹት በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሮኒክስ ለርኒንግ ዳይሬክተር ዶ/ር በኃይሉ ገ/ማሪያም፤ አገልግሎቱ ከጀመረ ወዲህ በኦንላይን ቀጥታ የትምህርትና ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደሀገር የተጀመረው የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና መልካም አጋጣሚ በመሆኑ የተገኘውን ዕድል ዜጎች በትጋት እንዲጠቀሙ ዶ/ር በኃይሉ መክረዋል፡፡
ከዚህ ጋር አያይዘው ዲጂታል ሚዲያ በኮምፒውተሮችና ተንቀሳቃሽ ስልኮች አማካይነት የተለያዩ መረጃዎችን ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ሰዎች እንደ መረጃ ምንጭነት መጠቀም እንዲችሉ የሚያደርግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
ከእነዚም ውስጥ ማህበራዊ ሚዲያ ሰፊውን ሽፋን የሚይዝና በተለይም ከ25 እስከ 35 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚጠቀሙ በ2024 በተደረገው ጥናት የተረጋገጠ ሲሆን በየዓመቱ 17 በመቶ እያደገ የሚሄድ መሆኑን የጥናቱ ግኝት ያመለክታል ብለዋል።
በፍጥነት ተደራሽና በስፋት የወቅቱን ገበያ እየተቆጣጠረ ከመሆኑም ባሻገር ለውሳኔ ሰጪነት እንደመረጃ ምንጭነት የሚያገለግል ነው ያሉት ዶ/ር በኃይሉ፤ ተፅዕኖ ፈጣሪ ስለሆነ ጠቀሜታው ሰፊና እያደገ የሚሄድ ነው ብለዋል።
የጾታ ስብጥርን መሠረት በማድረግ በተጠናው ጥናት በአብዛኛው ወጣት ወንዶች የሚጠቀሙ መሆናቸውን ጥናቱ ያመለክታል ያሉት ዶ/ር በኃይሉ ገብረ ማሪያም፤ በጥብቅ ዲስፕሊን ሊመራ ይገባል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከጠቀሜታው አንጻር በስፋት አገልግሎት ላይ እንዳይውል ተፅዕኖ ከሚፈጥሩ ጉዳዮች መካከል የኢንተርነት ዋጋ፣ ተደራሽነትና የቴክኖሎጂ እውቀት ውስንነት እንደሆኑ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ አገልግሎቱን ያለማግኘት ደግሞ ከዓለም አቅጣጫ ተቆርጦ እንደመቅረት ይቆጠራል ነው ያሉት፡፡
በአሉታዊ ጎኑ ደግሞ የተዛባ መረጃዎችን ማሰራጨት፣ ስም ማጥፋት፣ ለደህንነት ስጋት መሆን፣ ከዚያም ባለፈ በተከታታይ መጠቀም ለአዕምሮና ለአካላዊ ጤንነት ጉዳት ከማጋለጥ ባሻገር ከሰዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ውስን ስለሚያደርግ በማስተዋል ተግባራዊ ማድረጉ ይመከራል በማለት አሳስበዋል ዶ/ር በኃይሉ፡፡
ማህበራዊ ሚዲያን የሚጠቀሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተዓማኒነታቸው ያልተረጋገጡ መረጃዎችን እንደወረደ ከመጠቀም መቆጠብ አለባቸው ያሉት ዶ/ር በኃይሉ፤ ሐሰተኛ መረጃ ሲያጋጥም ወዲያው ማጋለጥ ወይም ሪፖርት ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ማህበራዊ ሚዲያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ተዓማኒነት ባለውና የአሰራር ሥርቱን ተከትለው ለሚያከናወኑት ፋይዳው የላቀ በመሆኑ በጥንቃቄ መጠቀም ይገባል በማለት ዶ/ር በኃይሉ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) መጭው ጊዜ ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ብርሃን የምንሸጋገርበት ብሩህ ዘመን መሆኑን ተናገሩ
በተቀሩት አጭር ቀናት ህብረተሠቡ የመራጭነት ካርዱን በመውሰድ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ የጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳና አካባቢው የፌደራልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጥሪ አቀረቡ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 25 ሺህ 338 ሊትር ቤንዝልና 62 ሺ 686 ሊትር ናፍጣ በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ