‎ከአየር ንብረት ተፅዕኖ ጋር እየተስተዋሉ ያሉትን ችግሮች ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ

‎ከአየር ንብረት ተፅዕኖ ጋር እየተስተዋሉ ያሉትን ችግሮች ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ

‎የደቡብ ኢትዮጰያ ክልል አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና የቀሪ ሶስት ወራት የተከለሰ ዕቅድ ግምገማ የሴክተር ጉባኤ በዲላ ከተማ አካሂዷል።

‎በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር)፤ የኢኮኖሚ ለውጥና የሰው ልጆች ዕድገት በመኖሩ በየአካባቢ ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ለመከላከል የተጀመሩ ለውጦችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

‎አክለውም ማህበረሰቡን ለብክለት ከሚያጋልጡና ከሚጎዱ ነገሮች አንዱ የፕላስቲክ ቆሻሻ በመሆኑ በአወጋገድና ከመከላከል ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አንስተው፤ እንደ ሀገር በተጀመረው የተራራ ልማት ኢኒሼቲቭ ሥራ ለውጦች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።


‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቴ ግጄ፤ ከአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ጋር በርካታ ችግሮች እየተስተዋሉ በመሆናቸው እነዚህን ለመታደግና ለመከላከል ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ አመላክተዋል።

‎እንደ ሀገር የተራቆቱ አካባቢዎችን በማልማት፣ ብዝሃ ህይወትን በመጠበቅ፣ የደኖች ጉዳትን በመቀነስ አካባቢውን ለዜጎች ምቹና ተስማሚ ከማድረግ አኳያ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ አካባቢን ከብክለት መጠበቅና መንከባከብ ይጠበቅብናል ሲሉ አቶ ግዛቴ አንስተዋል።

‎ለዓለም ስጋት ከሆኑ ነገሮች ዋነኞቹ የብዝሃ ህይወት መመናመን፣ የአፈርና ውሃ ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ በመሆናቸው በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት ሊሠሩ ይገባል ሲሉ አቶ ግዛቴ ተናግረዋል።

‎የተራራማ አካባቢዎች ልማት ኢኒሼቲቭ ተራሮችን በማልማትና በመንከባከብ፣ አካባቢን በማፅዳት የተጀመሩ ተግባራት ውጤታማ ቢሆኑም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ጉዳት እያደረሰ ስለሆነ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡

‎የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ በወጣው አዋጅ 1382/2017 መሠረት ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ተግባራት መጀመራቸውንም አብራርተዋል።

‎በተለይም አካባቢን ለመጠበቅና ከብክለት ለመከላከል የደንና የተራራ ልማት ሥራዎች ወሳኝ በመሆናቸው አሁን ላይ ያሉ ጅምሮችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያፈልግ በማንሳት፤ የደረቅና የፕላስቲክ ቆሻሻዎችን አወጋገድ በአዋጁ መሠረት ተግባራዊ ለማድረግ እየሠሩ እንደሆነ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

‎ዘጋቢ: ፅጌ ደምሴ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን