ሚሊዮኖችን እየገደለ ያለው የጉሮሮ ካንሰር መንስኤ እና መፍትሄው
ጉሮሮ እንደማንኛውም የሰውነት አካል በተለያዩ በሽታዎች ይጠቃል ። ቫይረስ ኢንፌክሽን (bacteria, fungi)፣ ቶንሲል፣ አንገት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች፣ ካንሰር፣ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የጉሮሮ መቆጣት፣ የጨጓራ አሲድ እስከ ላይኛው የጉሮሮ ክፍል መምጣትና የመሳሰሉት ጎሮሮን ከሚያጠቁት ህመሞች ውስጥ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ጉሮሮን ከሚያጠቁት በሽታዎች ውስጥ አንዱ የጉሮሮ ካንሰር መሆኑን በሀዋሳ አዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል ከአንገት በላይ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ቢኒያም ዓለማየሁ ከ.ደ.ሬ.ቴ.ድ “ዋናው ጤና” የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ባደረጉት ቆይታ ይገልፃሉ፡፡
ቋሚ የሆነ የጉሮሮ ካንሰር ምልክት በህክምናው የተረጋገጠ ጥናት ባለመኖሩ ታማሚው በቀላሉ ለማወቅ እንደሚያስችለዉ አክለው ያብራራሉ ዶክተር ቢኒያም፡፡
ለጉሮሮ ካንሰር እንደ መንስዔነት ከሚነሱ ውስጥም፤ የዕድሜ መግፋት (ከ50 በላይ ዕድሜ) ጋር ተያይዞ የዘረመል (genetics) ችግር፣ የቫይረስ ኢንፌክሽን (virus infection)፣ ለረጅም ጊዜ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ከፍተኛ የጨጓራ አሲድ በተደጋጋሚ ወደ ላይኛው የጉሮሮ ክፍል መምጣት እና ሲጋራና አልኮል አንድ ላይ ረዘም ላለ ጊዜ መጠቀም የሚያዘወትሩ ሰዎች የበለጠ ተጋላጭ ሲሆኑ በዚህም ወጣቶች የመጋለጥ ዕድል እንዳላቸው በዋነኝነት እንደሚጠቀሱ ዶክተሩ ያስረዳሉ፡፡
ምግብ የመዋጥ ችግር፣ የጉሮሮ ህመም፣ የድምፅ መቀየር (መጎርነን)፣ አልፎ አልፎ የሚከሰት ሳልና አንዳንድ ጊዜ በትንታ የሚመጡ ሳል በቋሚነት የማይጠፉ ምልክቶች የሽታውን አመላካች መሆናቸውን ይጠቁማሉ፡፡
ብዙ ጊዜ ካንሰሮች በባህሪያቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚከሰቱ እንዳልሆኑና ቀስ በቀስ የመለወጥ (የመቀያየር) ባህሪ የሚያሳዩ ሲሆኑ በዚህም ጊዜ ሰውነታችን በራሱ ወደ ካንሰር የሚቀየሩ ህዋሳትን (cells) ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ከቁጥጥሩ ውጭ በሚሆንበት ወቅት ካንሰር ወደ መባል ደረጃ እንደሚያደርስ ተናግረዋል፡፡
ወደ ህክምና ታማሚዉ በሚመጣበት ወቅት የካንሰር ምልክቶችን ለማወቅ ከሚያግዙት ውስጥም ዕድሜ፣ በሽታው የቆየበት ጊዜ፣ ሲደረጉ የቆዩ የህክምና ክትትሎችና ለውጣቸው፣ ተጋላጭነት (ሲጋራና አልኮል)ና አልፎ አልፎ በቤተሰብ የመከሰት ዕድል በከፊል ለመለየት ከሚያስችሉት ውስጥ ለአብነት እንደሚጠቀሱ ይገልፃሉ፡፡
በርካታ የጉሮሮ ካንሰር አይነቶች እንዳሉ የሚያነሱት ዶ/ር ቢኒያም የህመሙን መነሻ በመለየት የተለያዩ ምርመራ ሲደረግ ጉሮሮን መሰረት አድርገው የሚነሱ የመጀመሪያ (primary) እና ከሌላ አካባቢ የውስጠኛ ሰውነት ክፍል የሚመጡ ሜታ ስታቲክ ሁለተኛ (secondary) የሚባሉ የካንሰር አይነቶች እንዳሉ ይገልፃሉ፡፡
በባህሪ ደረጃ ልዩነት ሲኖራቸው እንደየ ካንሰሩ አይነት ረጅም ጊዜ ማለትም ከ10 እሰከ 15 ዓመት የፈጀ አለያም አጭር ጊዜ ከ3 እስከ 6 ወርና 1 ዓመት በመውሰድ በሽታው ከቆይታ በኋላ ሊከሰት እንደሚችልና እንደየ አይነታቸው አመጣጣቸውም እንደሚለያይ ያብራራሉ፡፡
ለበሽታው ከሚሰጡ ባህላዊ ህክምናዎች ጋር ተያይዞ ዶ/ር ቢኒያም ከሙያ ተሞክሯቸው አንፃር እንደገለፁት፤ መድኃኒቱ ፍቱንነቱ እንዳለ ሆኖ መቼ እና እንዴት ምንያህል መድኃኒቱን መወሰድና መሰጠት ያለበትን ጊዜ ባለማወቅ ትክክለኛዉን የህክምና ጊዜ ክትትልና ምርመራ በማራዘም ወደ ከፍተኛ የካንሰር ደረጃ እንዲደርስ የማድረግ ክፍተቶች እንዳሉት ያስገነዝባሉ፡፡
ከጉሮሮ ህመም ጋር ተያይዞ አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው በተለምዶ ቶንሲል ተብሎ የሚጠራው የህመም ዓይነት ከጉሮሮ ካንሰር ጋር ግንኙነት እንደሌለው የህክምናው ሳይንስ እንደሚያስረዳ አክለው ይገልፃሉ፡፡
#ለጉሮሮ ካንሰር የሚሰጡ ምርመራዎችና ህክምናው፤
የጉሮሮ ካንሰር ምርመራ ከአሁን በፊት ያሉ የህመም ወይም የህክምና ውጤቶችን መሰረት በማድረግ ባለሙያው ታካሚውን በአካል (physical examination) በማየት፤ በመንካት፣ በማዳመጥ እና በደም ምርመራና በቤተ ሙከራ (labratory) ቁስለቱ ከሚታይበት ቦታ ናሙና (sample) በመዉሰድ መለየት እንደሚቻል ያብራራሉ።
ዓለም አቀፍ የካንሰር የህክምና ቡድን አጠቃላይ መሰረታዊ ሁሉንም አይነቶች በሚባል ደረጃ የሚከፋፈሉበት የካንሰር ደረጃ እንደሚያስቀምጥ የሚያነሱት ዶ/ር ቢኒያም ከደረጃ 1 እስከ 4 እንዳሉና አብዛኛውን ጊዜ ከ95 ፐርሰንት በላይ የሚሆኑ ታካሚዎች 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ በሚሆኑበት ደረጃ ላይ ወደ ህክምና እንደሚመጡ ያስረዳሉ፡፡
የጉሮሮ ካንሰር ህክምና እንደ የህመሙ ደረጃ የሚለይ መሆኑን የሚገልፁት ዶ/ር ቢኒያም 1ኛ እና 2ኛ የካንሰር ደረጃ የሚባሉት ሙሉ ለሙሉ ያልተሰራጩ ሲሆኑ በምርመራ ተረጋግጠው ቁስለቱ ያለበትን ቦታ ሙሉ ለሙሉ በቀዶ ጥገና በመቁረጥ፣ በጨረር ህክምና የሚሰጡ ተመራጭ የሆኑ ህክምናዎች ሲኖሩት በዚህም የመዳን ዕድል እንዳላቸዉና እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ የተሰራጩና መጨረሻ ደረጃ ለደረሱ 3ኛ እና 4ኛደረጃ የሚባሉት ደግሞ የጉሮሮ ካንሰር በደም ስር የሚሰጥ (chemotherapy) ህክምና ተመራጭ መሆኑን ያብራራሉ፡፡
የጉሮሮ ካንሰር ህክምና በሚሰጥበት ወቅትም ከበሽታው ጋር ተያይዞ ኪሎ የመቀነስ፣ ተጓዳኝ የሆኑ በሽታዎች እንደ ስኳር፣ ግፊት ህመሞች ይከሰታሉ።
የተጠቀሱ ችግሮች በሚከሰቱበት ጊዜ እንደ ስነ-ምግብና የህክምና አገልግሎት እገዛ (እርዳታ) እንደሚያስፈልግ ነው የሚገለፁት ዶ/ር ዓለማየሁ፡፡
አዘጋጅ ፡ ብዙነሽ ዘውዱ
More Stories
በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ መሰራቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ
በኮሬ ዞን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው – የዞኑ ጤና ዩኒት
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግርና መዘናጋት በዞኑ የወባ በሽታ እንዲጨምር ማድረጉን የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ