በእንሰት ሰብል ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተእፅኖ የሚያሳድሩ በሽታዎችን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት አርሶ አደሩ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

በእንሰት ሰብል ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተእፅኖ የሚያሳድሩ በሽታዎችን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት አርሶ አደሩ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ የካቲት 06/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ በእንሰት ሰብል ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተእፅኖ የሚያሳድሩ በሽታዎችን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት አርሶ አደሩ የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አስገነዘበ።

በዞኑ የእንሰት አጠውልግ በሽታ በሰብሉ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የመፍትሄ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን መምሪያው አስታውቋል።

በኢትዮጵያ እንሰት ከ20 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ዋስትናቸውን የሚያረጋግጡበት ሰብል ነው።

ሰብሉ ድርቅን የመቋቋም አቅም ያለውና በሁሉም የአየር ንብረቶች ምርታማ መሆን የሚችል መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

ይሁን እንጂ የሰብሉን ምርታማነትና ውጤታማነት የበለጠ ለማሻሻል እየተደረገ ባለው ጥረት የእንሰት አጠውልግ በሽታ በሂደቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

ይህንኑ አስመልክተው በየሳምንቱ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ወልቂጤ ኤፍ ኤም 89.2 ሬዲዮ ጣቢያ በሚቀርበው አርሶ አደር ለአርሶ አደር በተሰኘው የቀጥታ ስርጭት መሠናዶ ላይ ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትልና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ካሳ የእንሰት አጠውልግ በሽታ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ብለዋል።

በሽታው በሰብሉ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንና ለአርሶ አደሩም ግንዛቤ የመፍጠር ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልፀዋል።

የተለያዩ የምርምር ማእከላትና ባለሙያዎች በበሽታው ባህሪያትና መከላከያ ዘዴዎች ዙሪያ ጥናቶችን ቢያደርጉም እስካሁን ባለው ሂደት ለበሽታው ዘላቂ መፍትሄና መድኃኒት አለመገኘቱን አቶ አክሊሉ ጠቁመዋል።

በሁሉም የጉራጌ ዞን አካባቢዎች እንሰት በስፋት እንደሚመረትና ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግልጋሎቶች ጥቅም ላይ እንደሚውል ያወሱት የመምሪያው ምክትል ኃላፊ፥ ይህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለውን ሰብል ከጉዳት መከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎና ጥረት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

በተለይ በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ያለው ጥልቅ ማህበራዊ ግንኙነትና የመረዳዳት እሴት ለበሽታው ስርጭት ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑን ያስረዱት አቶ አክሊሉ፥ በመሆኑም ለእንሰት ልማት ስራ ጥቅም ላይ የሚውሉ የግብርና መሣሪያዎችን ባለመዋዋስና በጥንቃቄ በመጠቀም ስርጭቱን መግታት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

በእንሰት ሰብል ላይ እያጋጠመ ያለውን ተግዳሮት በዘላቂነት በመከላከል “እንሰትን ከመጥፋት ወደ ማስፋት” በሚል መርህ በአሁኑ ጊዜ በዞኑ ያለውን 150 ሺህ ሄክታር የእንሰት ሰብል ሽፋን የበለጠ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተራ ስለመሆኑም አመላክተዋል።

በመሆኑም ከምግብ ዋስትና በላይ የማህበረሰቡ መገለጫና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውን የእንሰት ሰብል ምርታማነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ምክትል ኃላፊው አሳስበዋል።

በእለቱ በነበረው የቀጥታ ስርጭት መሠናዶ አድማጮች ከተለያዩ የዞኑ አከባቢዎች በመደወል በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተው በኃላፊው ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ዘጋቢ፡ አስቻለው ተስፋዬ – ከወልቂጤ ጣቢያችን