አርሰናል ከማንቸስተር ዩናይትድ አጓጊው ጨዋታ

አርሰናል ከማንቸስተር ዩናይትድ አጓጊው ጨዋታ

ሀዋሳ፡ ጥር 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በ23ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አርሰናል እና ማንቸስተር ዩናይትድ በኤምሬትስ ስታዲየም ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 ጀምሮ ተጠባቂ ፍልሚያ ያደርጋሉ።

አርሰናል መሪነቱን ለማጠናከር ማንቸስተር ዩናይትድ በበኩሉ በአውሮፓ መድረክ ተሳታፊ የሚያደርገውን ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ የሚያስችለውን አጋጣሚ ለመፍጠር ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የሚመራው አርሰናል በአራት ውድድሮች ጠንካራ ፉክክር በማድረግ ላይ ይገኛል።

መድፈኞቹ በሁሉም ውድድሮች ያለፉትን 12 ጨዋታዎች አልተሸነፉም።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ የዋንጫ ጥሙን ለማርካት በጠንካራ አቋም ላይ ይገኛል።

አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ በመጀመሪያ ጨዋታቸው በማንቹሪያን ደርቢ ማንቸስተር ሲቲን በአሳማኝ ብቃት ካሸነፉ በኋላ ለሌላ ከባድ ተልዕኮ ወደ ሰሜን ለንደን አምርተዋል።

በ35 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሪሚዬር ሊጉ ካለፉት 10 ጨዋታዎች ሽንፈት ያስተናገደው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

አርሰናል በኤምሬትስ ስታዲየም በሁሉም ውድድሮች ባለፉት 16 ተከታታይ ጨዋታዎች ሳይሸነፍ መጓዝ ችሏል።

ክለቡ በነዚህ ጨዋታዎች 38 ጎሎችን በተጋጣሚዎቹ መረብ ላይ ሲያሳርፍ የተቆጠረበት 7 ጎል ብቻ ነው።

ማንቸስተር ዩናይትድ በአንፃሩ ከሜዳው ውጪ ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች አላሸነፈም።

አርሰናል ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያከናወናቸውን ያለፉት 6 ጨዋታዎች ሽንፈትን አላስተናገደም።

በኤምሬትስ ስታዲየም የተደረጉት ያለፉት የእርስ በእርስ ግንኙቶች በመድፈኞቹ አሸናፊነት ነው የተጠናቀቁት።

ቀያይ ሰይጣኖች ከሜዳቸው ውጪ አርሰናልን ለመጨረሻ ጊዜ ካሸነፉ 8 ዓመታት አልፈዋል።

በአጠቃላይ ሁለቱ ክለቦች ከአሁን በፊት 245 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ዩናይትድ 99 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።

አርሰናል ደግሞ 91 ጊዜ ሲያሸንፍ 55 ጊዜ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ዋንጫ ካነሱ ዓመታትን ያስቆጠሩት ሁለቱ የዘመናት ተቀናቃኞች የሚያደርጉትን አጓጊ ጨዋታ ክራይግ ፓውሰን በዋና ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ