የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሙሉ ፓኬጅ ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለፀ

‎ሀዋሳ፣ ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) “የግብርና እምርታ ለዘላቂ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ የ2017/18 ሴክቶሪያል ጉባኤውን እያካሄደ ነው።

‎ግብርና ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ መሠረት ነው ያሉት የጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ማገሶ ማሾሌ ፤ በ2017 የምርት ዘመን የተመዘገቡ ምርጥ ተሞክሮችንና አፈጻጸሞችን በ2018 የምርት ዘመን በማጠናከር እንዲሁም የተስተዋሉ ጉድለቶችን በማረም ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

‎አክለውም ይህ ወቅት የመኸር ወቅት ጨርሰን ወደ በጋ መስኖ የምንሸጋገርበት በመሆኑ በ2018 በጋ መስኖ በስንዴና በሌሎች ሰብሎች እምርታ የምናስዘግብበት ነው ብለዋል።

‎ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) እንዳሉት ፤ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በሙሉ ፓኬጅ ተግባራዊ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል ።

‎ግብርና የኢኮኖሚ ጀርባ አጥንት ነው ሲባል እንደሀገርና እንደየአካባቢው ምቹ የአየር ፀባይ በመጠቀም ምርታማነትን በማረጋገጥ ሕዝቡን ከተረጅነት ማላቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል ዶ/ር ደምሴ ።

‎እንደጋሞ ዞን በእንስሳት እርባታ ፣ በፍራፍሬና በሌሎች ዘርፎች በ2017 የምርት ዘመን  እምርታዎች እንደተመዘገቡ የገለጹት ዶ/ር ደምሴ በእጃችን ያሉ ፀጋዎችን ትኩረት ሰጥቶ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል ።

‎በመድረኩ የ2017 ምርት ዘመን የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት አፈጻጸምና የ2018 ዕቅድ ሰነድ እየቀረበ ይገኛል።

‎ዘጋቢ: ሰለሞን አላሶ፦ከአርባምንጭ ጣቢያችን