የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚዎችን የመድኃኒት እጥረት ችግር ለመፍታት የጤና ተቋማት አገልግሎት ከመስጠታቸው በፊት ቅድመ ክፍያ በመስጠት መድኃኒት እና የሕክምና ቁሶችን እንዲያሟሉ እየተሠራ መሆኑን የኮሬ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ

በኮሬ ዞን ጤና መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አስተባባሪ ‎አቶ ዘሪሁን በሪሶ፤ እንደሚናገሩት፤ ሕብረተሰቡን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎቱ እየተሰጠ ነው።

‎የማህበረሰቡ ቅሬታ የነበረበትን የመድኃኒት እጥረት ችግር ለመፍታት ከ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ አካባቢ በኬሌ ከተማ የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት መከፈቱ እፎይታን እየሰጠ ነው የሚሉቱ አስተባባሪው፤ በርካቶች በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን መታወቂያ በነጻ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

‎በ2018 በጀት ዓመት በወረዳ ከተሞች ተጨማሪ የማህበረሰብ መድኃኒት ቤቶችን ለመክፈት በጀት ተይዞ እየተሠራ መሆኑንና ይህም የመድኃኒት እጥረትን ለመቅረፍ አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

‎በተጨማሪም በአዲሱ አሠራር የጤና ተቋማት አገልግሎት ከመስጠታቸው በፊት የቅድመ ክፍያ በመስጠት መድኃኒት እና የሕክምና ቁሶችን እንዲያሟሉ መደረጉንና ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ከማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ወደ ጤና ተቋማት መተላለፉን አመላክተዋል።

‎ይህም የጤና ተቋማት በገንዘብ እጥረት ምክንያት ይገጥማቸው የነበረውን የመድኃኒት አቅርቦት ችግር የሚፈታ ይሆናል ብለዋል።

‎አሁን ላይ ከአባላት እየተሰበሰበ ያለው የአገልግሎት ክፍያ ከአምናው ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ከወዲሁ ክፍያ በመፈጸም አባላት ማሳደስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

‎በ2018 በጀት ዓመት ከ41 ሺህ በላይ አባወራና እማወራዎችን አባል በማድረግ ለጤና መድን አገልግሎት ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በመሰብሰብ ለጤና ተቋማት አገልግሎት ክፍያ ለማዋል መታቀዱን አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል።

‎ዘጋቢ፡ እስራኤል ቅጣው – ከይርጋ ጨፌ ጣቢያችን