በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ተግቶ በመስራት ከድህነት መውጣት ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ተግቶ በመስራት ከድህነት መውጣት ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሁሉም በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ተግቶ በመስራት ከድህነት መውጣት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።

በክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ቢሮ አዘጋጅነት ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው ኤግዚቢሽንና ባዛር በሆሳዕና ከተማ በይፋ ተከፍቷል።

በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፤ ሁሉም በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ተግቶ በመስራት ከድህነት መውጣት ይገባል ብለዋል።

የሀገራችንን ዕድገት ለማረጋገጥ ከተያዙ ቁልፍ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የማኑፋክቸሪንግና የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሆኑን ጠቁመው የተሰማሩትም ወደ ላቀ ደረጃ ሊሻገሩ ይገባል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

በኢግዚቢሽኑ የታዩ የተለያዩ ምርቶች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር እንዳሻው፤ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካትና ማሻሻያዎችን በማድረግ ሊወጣ የሚችለውን ከፍተኛ የወጪ ምንዛሬ ማስቀረት ይገባል ብለዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር የኢኮኖሚ ሉኣላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሁሉ ዐቀፍ እንቅስቃሴ ላይ ኢንተርፕራይዞችና የአንቀሳቃሾች ሚና የላቀ ነው ብለዋል።

በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ወደ ሞዴልነት ደረጃ ሽግግር ያደረጉትን መፍጠር የተቻለ ሲሆን በክልሉ በጥቃቅን፣ በአንስተኛና በመካከለኛ 3 ሺህ 620 ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

በክልሉ ስራ አጥነትን ለመቀነስና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ እምቅ አካባቢያዊ ሀብቶችን በተገቢው ለመጠቀም በአዳዲስ የሪፎርም ዕሳቤዎች በመመራት ከ4 መቶ ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት 9 ወራት ለ3 መቶ 13 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት ኃላፊው።

በክልሉ በገጠር እና በከተማ በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ ከ25 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በክልሉ በሚገኙ በተለያዩ መዋቅሮች የደረጃ ሽግግር መስፈርት አሟልተው በጥቃቅንና በአንስተኛ ደረጃ 4 ሺ 9 መቶ 48 ኢንተርፕራይዞች ሽግግር አድርገው ከእነዚህም መካከል ለክልል ዕውቅና ብቁ የሆኑ 60 ሞዴል ኢንተርፕራይዞች ለዕውቅና በቅተዋል ነው ያሉት።

የዕድገት ደረጃቸውን ያጠናቀቁ ለክልሉ ብቁ የሆኑ በመካከለኛ 146፣ በከፍተኛ 5 በጠቅላላው 151 ኢንተርፕራይዞች ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገር ችለዋል ብለዋል።

በዕለቱም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ወደ መካከለኛ እና ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ዕውቅና የተሰጣቸው አንዳንድ ኢንተርፕራይዞች በበኩላቸው፤ ያገኙት ሽልማት ከዚህ በተሻለ በመስራት ከራሳቸው አልፈው ለሀገራቸው የተሻለ ነገር እንዲያበረክቱ የሚያነሳሳ መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል።

ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን