በወባ ተጠቂ በሆኑ አከባቢዎች የወባ ኬሚካል ርጭት እያከናወነ መሆኑ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ የወባ ተጠቂ በሆኑ አከባቢዎች የወባ ኬሚካል ርጭት እያከናወነ መሆኑን የከተማው አስተዳደሩ ጤና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በከተማው በተመረጡ 4 ቀጠናዎች 1ሺህ 475 ቤቶች ኬሚካል እንደሚረጩ ተጠቁሟል።
በዞኑ በተለይም በጉራፈርዳ፣ በደቡብ ቤንች፣ በሲዝ እና በሚዛን አማን ከተማ የወባ በሽታ የሚታይባቸው ሲሆን፥ ክረምቱን ተከትሎ በዞኑ ሁሉም በሚባሉ ወረዳዎች እና ከከተማ አስተዳደሮች የወባ በሽታ መከሰቱ ተጠቁሟል።
በዞኑ ከተመረመሩ ሰዎች 63 ከመቶ በወባ በሽታ የተያዙ መሆናቸው ተመልክቷል።
ወይዘሮ ገነት ተመስገን በሚዛን አማን ከተማ የሻሸቃ ቀበሌ ነዋሪ ስትሆን እሷም ሆነች ቤተሰቦቻ በተደጋጋሚ በወባ በሽታ እንደሚጠቁ ይናገራሉ። በየወሩ ለህክምና ብቻ ከአንድ ሺ እስከ ሁለት ሺ ብር እንደምታወጣ ገልጻ በሽታው በተደጋጋሚ እንደሚነሳ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ መምህር ፍቃዱ ደንበል በበኩሉ በወባ በሽታ እሱም ሆነ አንድ አመት ያልሞላው ህጻን ልጁ በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሚታመሙ ተናግረዋል።
በዚህ ምክንያት በየወሩ ለህክምና ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጣ ተናግሮ ካለው የኑሮ ውድነቱ ጋር ተዳምሮ ኑሮውን ይበልጥ ከባድ እንዳደረገበት ይናገራል።
የአማን ቀጠና አንድ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ትእግስት ታደለ በበኩሏ፥ በቀበሌዋ ወባ ወረርሽን ከተከሰተ በኋላ ያቆሩ ውሃዎችን የማፋሰስ እና የማዳፈን ስራ ከመስራት ባለፈ፥ አጎበር ስርጭት ማከናወናቸውን ተናግራለች። ከዚሁ በተጓዳኝ በሁለት ቀበሌያት በሚገኙ 681 አባወራ እና እማወራ ቤቶችን የኬሚካል ርጭት እያደረጉ መሆኑን ተናግራለች።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ግርማዬ ቤርሙስ በበኩላቸው፥ በዞኑ የወባ ወረርሽኝ በስፋት ከተከሰተባቸው ውስጥ አንዱ የሚዛን አማን ከተማ አስተደር ሲሆን በከተማው በ14 ቀጠናዎች እና በ4 ቀበሌዎች ወረርሽኑ መከሰቱን ተናግረዋል።
ይህንን ወረርሽን ለመከላከል ለህብረተሰቡ አጎበር ከማደል ባለፈ የማፋሰስ እና የማዳፈን ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
ወረርሽኙን ሙሉ ለሙሉ መቋቋም እንዲያስችል በከተማው ወባ ተጠቂ ከሆኑ የኢንዱስትሪ ቦታዎች እና በወባ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ላይ የኬሚካል ርጭት እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚዛን ማረሚያ ቤት፣ ዩኒቨርስቲን ጨምሮ 1ሺህ 475 መኖሪያ ቤቶች የኬሚካል ርጭት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡም ለተከታታይ ስድስት ወራት ኬሚካል በተረጨ ቤት ላይ ቀለም ይሁን ተመሳሳይ ነገር ባለማድረግና ከኬሚካል ርጭት ባለፈ አጎበር በተገቢው በመጠቀም የውሃ ማፋሰሻዎች በመስራት ራሳቸውን ከወረርሽኙ ሊጠብቁም ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በዚህ ዓመት 137 ቋሚና 452 ጊዜያዊ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በየደረጃው ባሉ የጤና ልማት ሰራዊት አማካኝነት ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎችና የአቤትና አኳቲን ኬሚካል ርጭት ስራ መሰራቱን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ አስታወቀ
በኮሬ ዞን የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት እየተሰጠ ነው – የዞኑ ጤና ዩኒት
የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአጎበር አጠቃቀም ችግርና መዘናጋት በዞኑ የወባ በሽታ እንዲጨምር ማድረጉን የኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ