የባርሴሎና ቀዳሚ ተመራጭ

የባርሴሎና ቀዳሚ ተመራጭ

የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና የሮበርት ሊቫንዶውስኪ ተተኪ ለማድረግ በእጩነት ከያዛቸው ተጫዋቾች መካከል ሀሪ ኬን ቀዳሚ ተጫዋች መሆኑ ተገልጿል።

ፖላንዳዊው አጥቂ ሮበርት ሊቫንዶውስኪ በካታላኑ ክለብ ያለው ኮንትራት በዚህ የውድድር ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል።

ባርሴሎናም የ37 ዓመቱን ተጫዋች ኮንትራት የማደስ ፍላጎት እንደሌለው በመዘገብ ላይ ነው።

የስፔኑ ሀያል ክለብ የአንጋፋውን አጥቂ ኮንትራት ከማራዘም ይልቅ ሌሎች አጥቂዎችን ለማስፈረም ማማተር የጀመረ ሲሆን ሀሪ ኬን ቀዳሚ ምርጫው መሆኑን ዘጋርዲያን አስነብቧል።

እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ለሌቫንዶውስኪ ተስማሚ ተተኪ እንደሚሆን ባርሴሎና አምኖበታል ተብሏል።

እንደ ፈረንጆቹ በ2023 ከቶትንሃም በ100 ሚሊዮን ፓውንድ የባቬሪያኑን ክለብ የተቀላቀለው ኬን የውል ማፍረሻው 57 ሚሊዮን ፓውንድ ነው።

የስፔኑ ሀያል ክለብ ይህንን የውል ማፍረሻ ለመክፈል ባለማመንታት በድጋሚ ሁነኛ አጥቂን ከባየርንሙኒክ ለማስፈረም ጥረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ባርሴሎና ሮበርት ሌቫንዶውስኪን በ2022 ከባየርንሙኒክ ማስፈረሙ አይዘነጋም።

በወቅቱ ለዝውውሩ ወደ 50 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ የዝውውር ሒሳብ ነበር የከፈለው።

ሊቫንዶውስኪ ባበርሴሎናን ከተቀላቀለ በኋላ በእስካሁኑ ቆይታ 108 ጎሎችን ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን 2 የላሊጋ ዋንጫዎችንም ማሸነፍ ችሏል።

የልጅነት ክለቡን ቶትንሃምን በመልቀቅ ባየርንሙኒክን የተቀላቀለው ሀሪ ኬንም በጀርመኑ ክለብ በስኬት የታጀቡ ጊዚያትን እያሳለፈ ይገኛል።

የእንግሊዝ የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የሆነው ሀሪ ኬን በክለቡ በእግር ኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ የመጀመሪያ ዋንጫውን ከማሸነፉ ባሻገር እስካሁን 113 ጨዋታዎችን በማከናወን 108 ጎሎችን በማስቆጠር የጀርመን ቆይታውን አሳምሯል።

ተጫዋቹ በዘንድሮው የውድድር ዓመትም በ17 ጨዋታዎች 23 ጎሎችን በማስቆጠር ለክለቡ ውጤታማነት ጉልህ ሚና በመወጣት ላይ ይገኛል።

ሀሪ ኬን የባርሴሎናን ጥያቄ በመቀበል የሚዛወር ከሆነ በሶስት የተለያዩ ሊጎች የመጫወት ዕድልን የሚያገኝ ይሆናል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ