ጤናማ እና አምራች ዜጋን ለመፍጠር በጤና ስፖርት ቡድኖች የሚሳተፍ ማህበረሰብ መገንባት ወሳኝ መሆኑን የጎፋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ገለጸ
በጎፋ ዞን ከህዳር ስድስት እስከ ታህሳስ 12 ፈታ የጓደኛሞች ዋንጫ ለሚሳተፉ 12 የእግር ኳስ ቡድኖች የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ በተበረከተበት ወቅት የጎፋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ተወካይ አቶ ሀብታሙ ገዛኸኝ፤ በከተማዋ ጤና ስፖርት ቡድኖች መስፋፋታቸው ከስፖርታዊ ውድድር ባለፈ ማህበራዊ ትስስር በማጎልበት ጤናማ አምራች እና ሰላማዊ ዜጋን ለመፍጠር ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
ፈታ የጓደኛሞች ዋንጫ አስተባባሪ አቶ ቻንድራ አወል በበኩላቸው፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአራት ከተሞች በሚገኙ 56 ቡድኖች በርካታ ስፖርተኞች በውድድሩ እንደሚሳተፉ ገልጸው ለአሸናፊ ቡድኖች የተለያዩ ማበረታቻ ሽልማቶች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡
የጤና ቡድን አባላቱ ለአካባቢያቸው ብሎም ለከተማዋ የስፖርት እድገት ከፈታ ጋር በጋራ ለመስራት ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀው በቀጣይ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደርግላቸው ገልፀዋል።
የጎፋ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ተወካይ አቶ ሀብታሙ ገዛኸኝ በበኩላቸው፤ ፈታ ካፕ በዞኑ ከሚገኙ የጤና ቡድኖች መካከል ለ12ቱ ቡድኖች ስላደረገው የትጥቅ ድጋፍ አመስግነው ማህበረሰቡ በጤና ስፖርት እንዲሳተፍ ዞኑ በትከረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ንቁ፣ ብቁ፣ ጤናማ እና አምራች ዜጋን ለመፍጠር የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ መገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመምሪያው የስፖርት ተሳትፎና ውድድር ቡድን መሪ አቶ ትኩ ተላይነህ ሕብረተሰቡ በግልም ሆነ በጤና ቡድን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማዘውተር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ከመከላከል ባሻገር ወንድማማችነትን የሚያጎለብት በመሆኑ የሁልጊዜ ተግባር ሊያደርጉት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ፈታ የጓደኛሞች ዋንጫ የከተማውን የስፖርት እንቅስቃሴ በማነቃቃት ወንድማማችነትንና አብሮነትን የሚያጎለብት መሆኑን በሳውላ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ተሻለ ይርዳው ገልፀዋል፡፡
የጤና ቡድን አባላት በበኩላቸው በጤና ስፖርት በመሳተፍ የጤና ጥቅሞች ማግኘታቸውን ተናግረው ለከተማዋ ሁለንተናዊ የስፖርት እድገት፣ ልማት እና ሰላም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
በጤና ስፖርት በመሳተፍ ሁለንተናዊ የጤና ጥቅሞች ማግኘታቸውን የሚናገሩት ተጨዋቾቹ፤ ፈታ የጓደኛሞች ዋንጫ አዘጋጆች በአካባቢው በመምጣት ላበረከቱት የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ዘጋቢ: አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ማንቸስተር ሲቲ የፊል ፎደን ውል ለማራዘም ስራ መጀመሩ ተገለፀ
ዎልቭስ ሮብ ኤድዋርድስን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ሾመ
በኢትዮጵያ ዋንጫ ቤንች ቡና ማጂ፣አርባምንጭ ከተማ፣ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ኢትዮጵያ መድህን ወደ ቀጣዩ ዙር አለፉ