በኢትዮጵያ ዋንጫ ቤንች ቡና ማጂ፣አርባምንጭ ከተማ፣ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ኢትዮጵያ መድህን ወደ ቀጣዩ ዙር አለፉ

በኢትዮጵያ ዋንጫ ቤንች ቡና ማጂ፣አርባምንጭ ከተማ፣ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ኢትዮጵያ መድህን ወደ ቀጣዩ ዙር አለፉ

የ2018 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት መካሄድ ሲጀምሩ ቤንች ማጂ ቡና፣ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ኢትዮጵያ መድህን ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ 3ኛው ዙር አልፈዋል።

ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ በሀዋሳ አርቴፊሻል ስታዲየም ከጋሞ ጬንቻ ጋር የተጫወተው ቤንች ማጂ ቡና 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ሚቀጥለው ዙር ተሻግሯል።

ለአቦሎቹ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል ፅዮን ተስፋዬ በ30ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል።

ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ወላይታ ድቻን ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ያገናኘው ጨዋታ በወልዋሎ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲን የማሸነፊያ ጎሎች ኮንካኒ ሀፊዝ እና ፍሬው ሰለሞን በሁለተኛው አጋማሽ አስገኝተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ የወቅቱ የኢትዮጵያ ዋንጫው ባለቤት ወላይታ ድቻ በሁለተኛው ዙር ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ከረፋዱ 4 ሰዓት ጀምሮ ኢትዮ ኤሌክትሪክን የገጠመው ኢትዮጵያ መድህን አማኑኤል ኤሪቦ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል።

እንዲሁም ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በዛው በአዲስ ስታዲየም አርባምንጭ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን በማሸነፍ ወደ 3ኛው ዙር ተሻግሯል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ጎል መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ መለያ ምት አምርቷል።

በተሰጠው መለያ ምትም አዞዎቹ 5ለ4 በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል።

ወደ 3ኛው ዙር ለማለፍ የሚደረጉት የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች በነገው ዕለትም በሀዋሳ፣ጅማ እና አዲስ አበባ ከተማ የሚካሄዱ ይሆናል።

ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ