የአፈርና ውሃ ጥበቃ ማዕከል ‘ብራይት’ የተሰኘ ፕሮጀክት በዞኑ በአባያ ተፋሰስ በተመረጡ ቀበሌያት ከ26 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተቀናጀ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።
በአካባቢው ከከፍታማ ስፍራዎች የሚነሳው ጎርፍ አባያ ሐይቅን በደለል ከመሙላት አልፎ እርሻ መሬታቸውን ይጎዳ እንደነበር በቀበሌው የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ልማት ሥራ ላይ ካገኘናቸው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር ሻሜና አሻግረ እና በረታ በርበሬ ይናገራሉ።
በመልማት ላይ የሚገኙ ተፋሰሶችን በባለቤትነት ከሰው እና ከእንስሳት ንኪኪ በመጠበቅ ላይ መሆናቸውንም አክለዋል።
እንዲያለሙት ተለክቶ የተሰጣቸውን የተጎዳውን መሬት በሳምንት ሶስት ቀን በተነሳሽነት እያለሙ መሆናቸውን የሚናገሩት ደግሞ ሻራ ጫኖ ቀበሌ አርሶ አደር ወርቅነሽ ደንደአ ገልጸዋል።
በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል የመሬትና የስርዓተ ምህዳር አገልግሎት ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር ይልቃል አንተነህ፤ የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተፋሰስ አስተዳደር ድጋፍ ለጠንካራ፣ አካታች እና ተስማሚ ለውጥ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም (ብራይት) ፕሮጀክት እየተከናወነ ያለው የተፋሰስ ልማት ነዋሪዎች ኑሮ ማሻሻል እና ለአየር ንብረት ለውጥ ስጋቶች የማይበገር አካባቢ ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸው ፕሮጀክቱ በስምጥ ሸለቆ ሃይቆች፣ በአባይ፣ አዋሽ፣ ኦሞ፣ ጊቤ እና ተከዜ ተፋሰሶች ላይ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በጋሞ ዞን በሐሬ ንዑስ ተፋሰስ ጫኖ ጫልባ፣ ሻራ እና ጨንቻ ዲታ በሚያለማው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ማዕከል ብራይት የተሰኘው ፕሮጀክት ከዞኑ ግብርና መምሪያ ጋር በመቀናጀት የተጎዱ ተፋሰሶችን በህብረተሰብ ተሳትፎ መልሶ እንዲያገግሙ እየሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
የለሙ ተፋሰሶችን በመንከባከብ እና በመጠበቅ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ህብረተሰቡ መጠበቅ እንዳለበት አስተባባሪው አሳስበዋል።
በጋሞ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሀላፊ እና የተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ወርቅነህ ካልሳ በአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራ ላይ ከ520 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሥራው በፕሮጀክት ደረጃ ታቅፎ እየተከናወነ መሆኑ የተጀመረውን የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ሥራ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርገውም አቶ ወርቅነህ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የሀዲያ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ለ2018 በጀት ዓመት ከ10 ቢልዮን ብር በላይ በጀት ለተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲውል በተገቢው እንደሚሠራ ገለፀ
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመንግስትን ወጪ ከማዳን ባሻገር ለህሊና እርካታ የሚሰጥ ተግባር መሆኑ ተነገረ
የተገኘው አንፃራዊ ሰላም የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ከማጠናከር ባለፈ ለረጅም አመታት በፀጥታ ችግር ያለማውን የማዕድን ሀብት በመጠቀም የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በማጂ ወረዳ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ