የተገኘው አንፃራዊ ሰላም የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ከማጠናከር ባለፈ ለረጅም አመታት በፀጥታ ችግር ያለማውን የማዕድን ሀብት በመጠቀም የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በማጂ ወረዳ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ

የተገኘው አንፃራዊ ሰላም የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ከማጠናከር ባለፈ ለረጅም አመታት በፀጥታ ችግር ያለማውን የማዕድን ሀብት በመጠቀም የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በማጂ ወረዳ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ

‎የህዝብ ለህዝብ ውይይቶችን በማጠናከር ዘለቄታ ያለው ሰላምን ለመገንባት ከአጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን በምዕራብ ኦሞ ዞን የማጂ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

‎አቶ ታደመ ኮመሩ የማጂ ወረዳ የዲዚ ብሄረሰብ ተወላጅና የሀገር ሽማግሌ ሲሆኑ በአካባቢው ለረጅም ዘመናት በሰላም እጦት ግጭቶች ዝርፊያና የግድያ ወንጀሎች ይፈፀሙ እንደነበር አውስተው አሁን ላይ በተደረገው የሰላም ዘመቻ የተዘጉ መንገዶች በቤሮና በማጂ አካባቢ ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ ባለፈ የእርስ በእርስ ግንኙነቶች እንዲጠነክሩና የገበያ ትስስር በመፍጠሩ አንፃራዊ ሰላም ማግኘት ችለናል ብለዋል።

‎አቶ ታደመ አክለውም፤ በወረዳው የማዕድን ሀብት ቢኖርም በፀጥታ ችግር ለረጅም አመታት መጠቀም እንዳልተቻለ ገልፀው አሁን በመጣው አንፃራዊ ሰላም ወደ ስራ መገባቱን ገልፀው አካባቢውን ከማልማት ባለፈ ለሰላሙ መፅናት ትልቅ አቅምን ያዳብራል ብለዋል።

‎አቶ እንድሪያስ ኒያንግ በማጂ ወረዳ የሰላም ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲሆኑ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ጎሪ ጌሻ ወረዳ ቤሮ ወረዳ ሱርማ እና ማጂ ወረዳ ከተውጣጡ የሰላም ኮሚቴዎች በማቋቋም በጋራ በመሆን እቅድ በማዘጋጀት በየወረዳ ህዝቡን ያሳተፈ ውይይቶችን በማካሄድ አንፃራዊ ለውጦች መመዝገብ መቻላቸውን ተናግረዋል።

‎ህዝቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆን ለማስቻል ፀረ ሰላም ሃይሎችን አጋልጠው እንዲሰጡ እና የህግ የበላይነት እንዲከበር ሰፊ ጥረቶች የተደረጉ መሆኑን የሚናገሩት አቶ እንድሪያስ፤ በዚህም አንዳንድ የተዘረፉ ከብቶች የተመለሱበት ዘራፊዎችንም ለህግ የማቅረቡ ስራ በመሰራቱ የተሻለ ግንኙነት የተፈጠረበት የማይታረሱ ቦታዎች ማልማት የተቻለበት ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው ብለዋል።

‎የማጂ ወረዳ ሰላም ፀጥታና ሚሊሻ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፍንታሁን ዘለቀ፤ በወረዳው ያለውን የሰላም ችግር በዘላቂነት ለማጎልበት በወረዳዎች በሁሉም ቀበሌዎች ላይ የሰላም ኮሚቴ ከማቋቋ ባለፈ ኩታ ገጠም ቀበሌዎችን ማገናኘት ማወያየት እንዲሁም በየአካባቢው የሚነሱ የወሰን መገፋፋቶችን መለየትና ከአጎራባች ዞኖች እና ወረዳዎች ጋር የሚሰሩ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመው ከደቡብ ኦሞ ኛንጋቶም እና ከሀና ጋር የፀጥታ መንስኤዎችን በመለየት የሰላም እሴቶች ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

‎አቶ ፍንታሁን አክለውም አሁን ላይ ከሀገር መከላከያ፣ ፖሊስ እና ሚሊሻ ጋር በመቀናጀት አካባቢው ላይ ሰላም ለማፅናት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ዘጋቢ፡ ዮናስ ወ/ገብርኤል – ከሚዛን ጣቢያችን