በአካል ጉዳተኝነት ተስፋ ባለመቁረጥ የተገኘ ስኬት
ወጣት መለሰ እዮብ ይባላል፤ ተወልዶ ያደገው በከምባታ ዞን ሀደሮ ከተማ ነው። እንደማንኛውም ህፃን በሰላም የተወለደ ቢሆንም የፖሊዮ ክትባት በአግባቡ ካለመውሰዱ የተነሳ የልጅነት ልምሻ አጋጥሞት እግሮቹ ላይ የአካል ጉዳት እንደገጠመው ይናገራል።
ካጋጠመው የአካል ጉዳት የተነሳ በሁለት ክራንች ድጋፍ ነው እንቅስቃሴ የሚያደርገው።
ራሱን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ “አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም” የሚል ጽንሰ ሀሳብ ይዞ ያደገው ባለታሪካችን፥ ልጅ እያለ ራሴን ልቻል በሚል ስሜት በትንሹ ቤተሰቡን ያስቸግር እነደነበር እና ገና ትንሽ እያለሁ አዲስ አበባ ሄጄ የሊስትሮ ስራ እየሰራሁ ጎን ለጎን የጭነት ዕቃ ድለላም እሞክር ነበር ይላል።
ከጊዜ በኋላ ይጠቀምበት የነበረው ክራንች በመሰበሩ ምክንያት ብዙ ችግር ውስጥ መግባቱን ያስታውሳል።
ከዕለታት አንድ ቀን ግን የክራንቹን መሰበር የተመለከተ አንድ ግለሰብ ወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል ክራንች ታገኛለህ የሚል ጥቆማ ሲሰጠኝ ወዲያው ወስኜ ለቤተሰቤ እንኳን ሳልናገር የትራንስፖርት መኪና ለምኜ ወደ ሶዶ ከደረስኩ በኋላ አካል ጉዳተኛ እና ገና ልጅ መሆኔን ያዩ የጥበቃ ሰራተኞች ወደሆስፒታሉ እንዳልገባ ከለከሉኝና ከፍቶኝ ተመለስኩ ይላል።
ግን ደግሞ ተስፋ ሳልቆርጥ ዳግመኛ በሁለተኛ ቀን ሄጄ የውጭ ዜጋ በሆኑት በሆስፒታሉ ዶክተር አንደርሰን እይታ ውስጥ ገባሁና ይግባ ብለው ተቀበሉኝና ከክራንች ባለፈ የህክምና እና ሌሎች ድጋፎችን የማግኘት እድል አገኘሁ ይላል ባለታሪካችን።
በወቅቱ የነበረውን የልጅነት ቅልጥፍናውንና የይቻላል ስሜቱን የተረዱት ዶክተር አንደርሰን እዚያው የመኖር እና የተለያዩ ስራዎችን የመስራት እድል እንዲሰጠው አድርገው ሌሎች አካል ጉዳተኞችን የማስተማር ኃላፊነት እንደተሰጠውም ወጣት መለስ ይገልጻል።
ትምህርቴን በመቀጠል እና የአካል ጉዳተኞች ማህበር በመመስረት “አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም” በሚል ፅንሰ ሃሳብ በህይወታቸው ተስፋ የቆረጡ በርካታ አካል ጉዳተኞች ተስፋቸውን ማደስ መቻላቸውን የሚናገረው ባለታሪኩ በአሁኑ ጊዜ በማኔጅመንት የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቆ ሆስፒታሉ ረዳት ወጌሻ) (Asistant Physiotherapist) በመሆን እንደሚሰራ አስረድቷል።
ዛሬ ላይ እሱ በፈጠረላቸው ግንዛቤ በርካቶች ህይወታቸው ተቀይሯል፤በሀደሮ ከተማ ብቻ በየቤታቸው ተደብቀው የኖሩ አካል ጉደተኞች የህክምና ዕድል ተመቻችቶላቸዋል።
በፈጠራ ስራ አምናለሁ የሚለው ወጣት መለስ በአንድ ወቅት ክርስቲያን ሆስፒታል የክረንች አጥረት ሲያጋጥም 4መቶ ክራንቾችን በእጁ ጥበብ በመስራት ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት መቻሉን ይናገረል።
በተጨማሪም በወላይታ ሶዶ ለሚገኘው ለኦቶና ሆስፒታል በአንድ ጊዜ 40 አልጋዎችን በመጠገን በስራ ላይ እንዲውል ማድረጉንም ይናገራል።
የሰው ልጅ እችላለሁ ካለ የማይሰራው ስራ የለም የሚል አቋም ያለው ወጣት መለስ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች የአካል ጉዳተኞች ማዕከላትን እገነባለሁ፤ ወላይታ ሶዶ እና ሀዋሳ ከተማም ክረንችን ጨምሮ የተለያዩ ዕቃዎች ማምረቻ ማዕከል በማቋቋም ለበርካታ አካል ጉዳተኞች የስራ እድል መፈጠሩንም ይገልፃል።
አካል ጉዳተኝነት በተለያዩ መነሻ ምክንያቶች ይገጥማል የሚለው ወጣት መለስ ምክንያቶችን ከማሰላሰል ይልቅ ጉዳቱን በጸጋ ተቀብሎ ለቀጣይ የተሻለ ህይወት መትጋት እንደሚያስፈልግም ምክረ ሀሳቡን ይሰጣል።
“ገና የስኬት ጉዞዬ ጅማሮ ላይ ወደክርስቲያን ሆስፒታል እንደልገባ በተከለከልኩ ሰዓት ተስፋ ቆርጬ ያለመመለሴ ወደተሻለ ህይወት መራኝ” የሚለው ባለታሪኩ ልክ እንደእኔ ተስፋ መቁረጥና ያለመቻልን ጥሶ በማለፍ “እችላለሁ”ማለት የስኬት መነሻ እንደሚሆን ይናገራል።
በአሁኑ ጌዜ “በይቻላል! መንፈስ” በወላይታ ሶዶና በሀደሮ ከተማ ባቋቋምኩት የተለያዩ እቃዎች ማምረቻ ማዕከል ብቻ ከ30አስከ 40 ለሚሆኑ አካል ጉዳተኞች የስራ እድል በመፍጠር ውጤታማ መሆናቸው አካል ጉዳተኞች ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ለመትረፍ መቻላችንን ያስመሰክርንበት አንዱ መንገድ ነው ይላል።
ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የስራ ሁኔታ እና ቦታ በመፍጠር ለሌሎች የመፍትሄ ሰው መሆን የወደፊት ህልሙ መሆኑንም ነግሮናል።
በተለያዩ ምክንያቶች ያልወጡ አካል ጉዳተኞችን ህብረተሰቡ እና መንግስት ከቤት እንዲወጡ ማበረታታት እና
በማህበረሰቡ ውስጥ ካለው የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ ወደኋላ እንዳይቀሩ በጋራ እንስራ የሚለው የባለታሪኩ የሀሳቡ መቋጫ መልዕክት ነው።
ዘጋቢ፡ ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የተገኘው አንፃራዊ ሰላም የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ከማጠናከር ባለፈ ለረጅም አመታት በፀጥታ ችግር ያለማውን የማዕድን ሀብት በመጠቀም የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በማጂ ወረዳ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ
ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ የውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
የህፃናትን ጤናማነት ለመጠበቅ ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ