ሀዋሳ፡ ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቆጎታ ወረዳ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በበጀት ዓመቱ ከ 98 ሚሊዮን 311 ሺህ በላይ ብር በውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በበጀት ዓመቱ ለወረዳው ከተመደበው 188 ሚሊየን ብር ውስጥ 57 ከመቶ የሚሸፈነው ከውስጥ ገቢ መሆኑ ተጠቁሟል።
አቶ ቶፋ ቶርቦባ እና ሳሙኤል ቢጆ በቆጎታ ወረዳ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ገልጸው፥ ግብር ለሀገር ክብርና ለአከባቢው እድገት የሚከፈል በመሆኑ በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።
እኛ ግዴታችንን ተወጥተን በአከባቢው የመሰረተ ልማት ስራ በአግባቡ እንዲከናወን መብታችንን እንጠይቃለን ያሉት ግብር ከፋዮቹ ለዚህም ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ በአግባቡ ግብርን መክፈል እንዳለበት መክረዋል ።
በወረዳው በመደበኛ 82 ሚሊየን 436 ሺህ 933 ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በሩብ ዓመቱ 14 ሚሊየን 308ሺህ 768 ብር መሰብሰቡን ጠቁመው ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 15 ሚሊየን 74ሺህ 500 ብር ለማሳካት ታቅዶ በሩብ ዓመቱ 1 ሚሊዮን 906 ሺህ 12 ብር መሰብሰቡን አብራርተዋል።
የቆጎታ ወረዳ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ግዛቸው በበጀት ዓመቱ 98 ሚሊዮን 311 ሺህ 451 ብር በውስጥ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በጊዜ እንዲከፍል ጠይቀዋል ።
በወረዳው የተለያዩ የመሠረተ ልማት ስራዎችን ለማከናወን ሀብት ያስፈልጋል ያሉት የቆጎታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አየለ ቱንጄ ፤ በበጀት ዓመቱ ለወረዳው ከተመደበው 188 ሚሊየን ብር 57 ከመቶ የሚሸፈነው ከውስጥ ገቢ ነው ብለዋል ።
ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ይህንን ተረድቶ የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡ እና በታማኝነት መክፈል አለበት ያሉት አቶ አየለ ፤ የወረዳው መንግስት በዚያው ልክ የመሰረተ ልማት ስራውን ለማከናወን ጥረት ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል ።
በጋሞ ዞን ገቢዎች መምሪያ የትምህርትና ስልጠና ባለሙያ አቶ ብርሀኑ ተስፋዬ በዞኑ የሚገኙ ግብር ከፋዮች ግብርን በወቅቱና በአግባቡ እንዲከፍሉ ተከታታይነት ያለው ትምህርት በመሰጠቱ የተሻለ አፈፃፀም እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል ።
በቆጎታ ወረዳም የሚገኙ ግብር ከፋዮች በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ በግዜ ግብር እንዲከፍሉ እየተደረገ እንደሚገኝ አቶ ብርሀኑ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ ፡ ተመኙህ ገረሱ -ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የህፃናትን ጤናማነት ለመጠበቅ ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
በኮሬ ዞን የአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መልሶ የማደራጀት ምክክር መድረክ ተካሄደ