የህፃናትን ጤናማነት ለመጠበቅ ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀድያ ዞን የምሻ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የህፃናትን ጤናማነት ለመጠበቅ ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በወረዳው ሞርሲጦ ከተማ ጤና አጠበበቅ ጣቢያ ልጆቻቸውን ሲያስከትቡ አግኝተን ካነጋገርናቸው ወላጆች መካካል ወ/ሮ ተስፋነሽ ገለቶ፣ ራሄል መለሰ እና ቆንጅት ኤልያስ የልጆቻቸውንና የራሳቸውን የግል ጤና ከመጠበቅ ጀምሮ ለህጻናት አቅም በፈቀደ መጠን የአመጋገብ ስርዓት ለማስተካከል እየተጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ለዚህም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከጤና ባለሙያዎች የሚያገኙት የንጽሕና አጠባበቅና የአመጋገብ ስርዓት ማስተካከል ዙሪያ ያገኙት ግንዛቤ እንደገዛቸው ተናግረዋል።

በሞርሲጦ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ የእናቶችና የህጻናት የክትባት አገልግሎት ባለሙያ እና የህጻናት ጤና አጠባበቅ ዘርፍ አስተባባሪ ወ/ሮ ሽቱ በየነ የህጻናት ጤና አጠባበቅ ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ የሚሰጥ አገልግሎት እንደሆነ ጠቁመዋል።

ወ/ሮ ሽቱ አክለውም በድህረ ወሊድ ወቅት የእናት አመጋገብ በልጅ ጤና ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን አንስተው፥ ህጻናት ከ 6 ወር በኋላ ከእናት ጡት በተጨማሪ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ለህጻናት ጤናማ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።

ህጻናት እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ለባክቴርያ የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው ያሉት ደግሞ የጤና አጠበበቅ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ደገለ ወ/ጊዮርጊስ ናቸው።

በዚህም በሽታ የመከላከል አቅማቸውን ለማሳደግ እና ጤናማ የሆነ ዕድገት እንዲኖራቸው ለማስቻል ህጻናትን መደበኛ የክትባት አገልግሎት እንዲያገኙ እንደጤና ጣቢያው በቀጠሮ መሰረት የቤት ለቤት ክትትልና ቅስቀሳ እየተደረገ ስለመሆኑም አንስተዋል።

የምሻ ወረዳ ጤናጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኤርጉዶ በበኩላቸው የህፃናትን ጤናማነት ለመጠበቅ ከቅድመ ወሊድ ክትትል ጀምሮ ለነፍሰጡር እናቶች የግንዛቤ ስራ እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጤናማ ልጅ እንዲኖር የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት መጠቀም ወሳኝነት እንደለው የጠቆሙት ኃላፊው ለወላጆች በቅድመ ወልድ እና በድህረ ወልድ ወቅት የምክር አገልግሎት በተገቢ እንደሚሰጣቸው ጠቅሰዋል።

ልጆችን በአግባቡ ማስከተብ፣ የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ፣ ንጽህናቸውን መጠበቅ እና በዕድሜያቸው ልክ እያደጉ መሆናቸውን መከታተል ተገቢ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው በተለይ በህጻናት ላይ የጤና ዕክል ከገጠማቸው ከባህላዊ ህክምና ይልቅ ወደ ጤና ተቋማት በፍጥነት መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ዘጋቢ: ሳምራዊት ያዕቆብ – ከሆሳዕና ጣቢያችን