በከተማ እና በገጠር ልማት መካከል ያለውን ትስስር ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ
የጋሞ ዞን ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድ ላይ የምክክር መድረክ በማካሄድ ላይ ነው።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት፤ መድረኩ በጋሞ ዞን በተለያየ ፈርጅ ደረጃ የሚገኙ ከተሞችን የወደፊት ሁኔታ በመቅረጽ የኢኮኖሚ አድገት እና ማህበራዊ ለውጥ ሞተር ሆነው የሚያገለግሉ ጠንካራ እና ዘላቂ ከተሞችን ለመገንባት ያለመ ነው፡፡
በከተማ እና በገጠር ልማት መካከል ያለው ትስስርን ማረጋገጥ የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑን በመረዳት አስፈላጊውን ትኩረት አግኝቶ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።
የልማት ኮሪደሮች እንደ ወሳኝ የህይወት መር ሆነው ያገለግላሉ፤ በከተማ-ገጠር ኮሪደሮች ላይ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ኢንቨስት በማድረግ የተመጣጠነ ልማትን ለማነቃቃት ጥረት ይደረጋል ነው ያሉት።
የመንገድ ኔትወርኮችን፣ የትራንስፖርት ግንኙነትን እና የኢንዱስትሪ ትስስርን ለማስፋፋት መግስት የበኩሉን ጥረት ያደረጋል ነው የተባለው።
የጋሞ ዞን ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አርጋው በመድረኩ ባስተላለፉት መልእክት እንዳሉት፤ ከተሞች በነዋሪዎች ባለቤትነትና ንቁ ተሳትፎ እንዲለሙ በተሰራው በዞኑ የከተሜነት እድገት 28 በመቶ የደረሰ ቢሆንም ከክልል አማካይ ረገድ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለሚገኝ በከተማ ማስፋፋት ላይ መስራት ያስፈልጋል።
በገጠርና በከተማ መሰረተ ልማት ግንባታ ረገድም ተጨባጭ ለውጥ የተመዘገበበት አመት መሆኑን አመላክተዋል።
ከተሞች ከፈርጃቸው አንጻር በተጣጣመ መልኩ በፕላን እንዲመሩ በካዳስተር ሲስተም ዘርፉን ለማዘመን ጥረት መደረጉን ጠቅሰዋል።
ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 206 ሄክታር መሬት ለማዘጋጀት ታቅዶ 806 ሄክታር ለማሳካት መቻሉን ገልጸው ለስኬቱ በማስፋፊያ አካባቢ ሳይፈቀድ የተያዙ ቦታዎችን በህጋዊ መንገድ መፍታት በመቻሉ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ: አሰግድ ተረፈ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የባስኬቶ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 10ኛ አመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን አካሂዷል
በቫሌንሽያ ግማሽ ማራቶን አትሌት ዩሚፍ ቀጄልቻ አሸነፈ
የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በማስፋፋት የአየር ንብረት ብክለትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነው