የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በማስፋፋት የአየር ንብረት ብክለትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነው
በዲላ ዩኒቨርሲቲ “NORHED-II ENERGY” ፕሮጀክት ከጌዴኦ ዞን ውሃና ማዕድን ኢነርጂ መምሪያ ጋር በመቀናጀት ለአማራጭ ኢነርጂ ባለሙያዎች የሶላር ጥገና ስልጠና ሰጥቷል፡፡
“NORHED-II-ENERGY” ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ሴቶችንና አቅመ ደካማ አረጋውያንን ለመደገፍ እ.አ.አ 2021 ሰራውን የጀመረ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የፕሮጀክቱ አስተባባሪና በዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ ገዛኸኝ ከበደ የተናገሩት፡፡
በአማራጭ ኢነርጂ በጌዴኦ ዞን በዘርፉ ለሚሰሩት ባለሙያዎች የሶላር ጥገና ስልጠና በመስጠታቸውን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገልፀዋል፡፡
ባለሙያዎቹም በንድፈ ሀሳብ ያገኙትን ስልጠና በተግባር እንዲያሳዩ በዲላ ዙሪያና በወናጎ ወረዳ በአንዳንድ ጤና ተቋማትና በይርጋጨፌ ወረዳ በፀሐይ ሀይል ውሃ የሚስቡ ሶላሮች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት እንዲስተካከል የመፍትሄ ሀሳቦችን ባለሙያዎቹ ማስቀመጣቸውን መምህርና ተመራማሪ ገዛኸኝ አስታውቀዋል፡፡
የጌዴኦ ደን አጠባበቅ “ባቦ” ስርዓት ለማስቀጠል አማራጭ ኢነርጂ በአግባቡ በመጠቀም በዓለም ቅርስነት በዩኒስኮ የተመዘገበውን ሀብት ለማስጠበቅ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን የጌዴኦ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ ዳዊት ጀቦ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
እንደ ጌዴኦ ዞን ከ80 በላይ ቀበሌያት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽ ስላልሆነ ሶላርና ማገዶ ቆጣቢ ለህብረተሰቡ ለማዳረስ በትኩረት እየተሰሩ መሆናቸውን ኃላፊው በመጥቀስ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ላደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ፣ ባዮ ጋዝና በፀሐይ የሚሰሩ ሶላሮችን በማሰራጨት በአጠቃቀም ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማሰጨበጫ ትምህርት በመስጠት ድጋፍና ክትትል ማድረጋቸውን የጌዴኦ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ የአማራጭ ኢነርጂ ተክኖሎጂ ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ ከበደ ተናግረዋል፡፡
ማገዶ ቆጣብ ምድጃዎች የጊዜና የጉልበት ብክነት ከመታደግ ባለፈ በሴቶችና ህጻናት በጭስ ምክንያት በአየር ብክለት ሊከሰቱ የሚችሉትን በሽታዎች ለመቀነስ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አቶ ብርሃኑ በመናገር ይህን ለማጠናከር በዲላ ዩኒቨርሲቲ “NORHED-II ENERGY” ፕሮጀክት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን አብራርተዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የባስኬቶ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር 10ኛ አመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን አካሂዷል
በከተማ እና በገጠር ልማት መካከል ያለውን ትስስር ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ
በቫሌንሽያ ግማሽ ማራቶን አትሌት ዩሚፍ ቀጄልቻ አሸነፈ