የረዥም ጊዜ ጥያቄ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በመብቃታቸው መደሰታቸውን በኮንሶ ዞን የካራት ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

የረዥም ጊዜ ጥያቄ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በመብቃታቸው መደሰታቸውን በኮንሶ ዞን የካራት ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

‎በተከናወኑ የልማት ተግባራት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑንና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።

‎ከካራት ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ንጋቱ ኩልኩላና አቶ አብርሀም ያቤሎ፤ በከተማው የረዥም ጊዜ የህዝቡ ጥያቄ የነበሩት የውስጥ ለውስጥ መንገድና የድልድይ ስራ መጠናቀቃቸው ለጥያቄያችን ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል።

‎ዶ/ር ዮናስ ሮባዮና አቶ ኩሴ ኩርታይሌም፤ ከተማው ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መሆኑንና በተለይ ደረጃውን የጠበቀ የቄራ አገልግሎት መገንባቱ የህብረተሰቡን ጤና ከመጠበቅ አኳያ አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

‎በቀጣይም እንደ ከተማ ነዋሪ ለልማት ስራ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ገልፀው የመብራትና መሠል ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

‎የካራት ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት የተቀናጀ የከተሞች መሠረተ ልማት ባለሙያ አቶ በረከት በላቸው፤ በከተማው በህብረተሰብ ተሳትፎ በርካታ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

‎በተለይም በውስጥ ለውስጥ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የዲችና የድልድይ ስራ በስፋት መከናወኑ የህብረተሰቡን የብዙ ጊዜ ጥያቄ የመለሰ መሆኑን አመላክተዋል።

‎ደረጃውን የጠበቀ የቄራ አገልግሎት ተገንብቶ መጠናቀቁንና በቅርብ ቀን ወደ ስራ የሚገባ እንደሆነ ጠቅሰው ከመብራት አገልግሎት አኳያ የሚታየውን ውስንነት ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ብለዋል።

‎የካራት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ያቤሎ ኩሴ፤ በአመራሩና በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የጤና ኬላዎችና የመሠረተ ልማት አውታሮች ተገንብተው ተጠናቀዋል።

‎የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የነበሩት የቄራ አገልግሎትና የድልድይ ስራ መጠናቀቅ በቅርቡም ለአገልግሎት የሚበቃ መሆኑን ተናግረዋል።

‎በቀጣይ ህብረተሰቡም ለልማቱ ተሳትፎ ከማድረግ ባሻገር የተሰሩ መሠረተ ልማቶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል ከንቲባው።

‎ዘጋቢ: ማርታ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን