የዲዚን ህዝብ ባህል ታሪክና ማንነትን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ለትውልድ ማሰተላለፍ እንደሚገባ የዲዚና አካባቢዋ ምሁራን ማህበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ መቱ አኩ ገለፁ
ማህበሩ በማጂ ወረዳ ቱም ከተማ ላይ የ2017 አፈፃፅምና እና 2018 ዕቅድ ላይ ውይይት በማድረግ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።
የዲዚና አካባቢዋ ምሁራን ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የማህበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ መቱ አኩ፤ የዲዚን ህዝብ ባህል ታሪክና ማንነትን በለውጡ መንግስት የብልፅግና እሳቤ በራሳችን እውቀት ያሉንን ተፈጥሮአዊ ሀብቶችን በጥናትና ምርምር በማስደገፍ ማበልፀግ እና ለትውልድ ማሸጋገር ዋነኛ የማህበሩ አላማ ነው ብለዋል።
አቶ መቱ አክለውም፤ የነገው የዲዚ ህዝብ ማንነቱ የተከበረለት ታሪክና ህብረተሰብ ተፈጥሮ ባህልና እሴቱን በመጠበቅ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ትውልድን በማገናኘት በጋራ የምንበለፅግበት ነው ብለዋል።
የምሁራን ማህበሩን የ2017 ዓ.ም አፈፃፀም ያቀረቡት የምሁራን ማህበሩ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አዲስ ምዕራፍ አለሙ፤ ማህበሩ በዋናነት የአባላቱን ቁጥር ከነበረበት ወደ 5000 ለማሳደግ እና 50 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን ገልፀው በዚህም 1499 አዲስ አባላትን ከማፍራት ባለፈ 3 ሚሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
አፈፃፀሙ 23 ፕርሰንት ላይ እንደሆነ የተናገሩት አቶ አዲስ ምዕራፍ፤ በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችን በማሰባሰብ ማህበሩን ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ከምሁራን መካከል ዶ/ር አብረሀም ታምራት፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጤና ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር እና ተመራማሪ የዲዚና አካባቢው ላይ ያሉ ችግሮችን በመለየት በአካባቢው የሚገኘውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እውቀትን መሰረት በማድረግ ለውጥ ለማምጣት የተቋቋመና እየሰራ የሚገኝ ማህበር ነው ብለዋል።
ሌላኛው የምሁራን አመራር የበላይ ጠባቂ አቶ ገመዳ ከይዳድ፤ ማህበሩ ለዲዚ ህዝብ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የሆኑ ችግሮችን በትምህርት በጤና በግብርና ለመፍታት የተቋቋመ ማህበር መሆኑን ተናግረው ለዚህም ማህበሩን በሀብት ማደራጀት ይገባል ብለዋል።
አቶ በድሉ መዓዛ የማህበሩ ምክትል ጠባቂ በበኩላቸው፤ የዲዚ ማህበረሰብ በሶስት መዋቅሮች እንደሚገኝ ገልፀው ቤሮ ወረዳ ማጂ ወረዳ እና በቱም ከተማ አስተዳደር በእነዚህ ውስጥ ያሉ ነባር ብሄረሰቦች በአንድ ላይ ያቀናጀ ነው ብለዋል።
የዲዚ ህዝብ ባህሉና ቋንቋውን እንዲያሳድጉ እንዲሁም ለታሪክ ሊበቁ የሚችሉ ያልተፃፈላቸው ያልተነገረላቸው በርካታ በሀገራችን መዛግብት ሊመዘገቡ የሚችሉ ቢኖርም በምሁራን ባለመታገዙ ወደ ኋላ መቅረቱን ተናግረው፤ ምሁራኑ ታሪካዊ የሆኑትን በጥናት በማስደገፍ ለህዝብና ለሀገር በማቅረብ ሁሉም እንዲያውቅና እንዲማርበት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የእለቱ የክብር እንግዳ እና የምዕራብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታምሩ ቦኒ በማጠቃለያው እንደገለፁት፤ ይህ የምሁራን ሀይል አንድ ሲሆን ምን ያክል ተፅእኖ ሊፈጥር እንደሚችን ማሳያ ናችው ብለው ያለንን እምቅ ፀጋ ወደ ሀብት በመቀየር የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።
አቶ ታምሩ አክለውም፤ የዲዚና አካባቢዋ ምሁራን ስያሜው ቀጥተኛ በመደመር የሚያምን ወንድማማችነትን ያነገበ በመሆኑ የራሱን ማንነት በባህሉ ቋንቋና እሴቱን በመጠበቅ ምሁራን አበክረው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
በእለቱ የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የዲዚ ልዩ ተወካይ አቶ እሸቱ ገ/ማርያም፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የዞንና ወረዳ አመራሮች፣ የዲዚ ዕውቅ ባላባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
ዘጋቢ፡ ዮናስ ወ/ገብሬኤል – ከሚዛን ጣቢያችን

More Stories
በከተማ እና በገጠር ልማት መካከል ያለውን ትስስር ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ
በቫሌንሽያ ግማሽ ማራቶን አትሌት ዩሚፍ ቀጄልቻ አሸነፈ
የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በማስፋፋት የአየር ንብረት ብክለትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነው