ከማን ምን ይጠበቃል?

በካሡ ብርሃኑ

እንደ ሃገር ግጭቶች እዚም እዛም እየተነሱ የብዙዎች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡

እነዚህ ግጭቶች በተለይ ከለውጡ በፊት በነበሩ ጥቂት የማይባሉ ዓመታት አንዴ በብሄር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሃይማኖት ሰበብ እየተፈጠሩ በኢትዮጵያ ያለው ማህበራዊ ሰላም እንዲናጋ አድርገዋል፡፡ ይህን የሰላም መናጋት ተከትሎ በወቅቱ ገዢ የነበረውን ፓርቲ ከግንባርነት ወደ ውህድ ፓርቲነት በመቀየር አዲስ አመራር እንዲመጣ አድርጓል።

ይሁን እንጂ ባለፉት አራትና አምስት የለውጥ ዓመታት ችግሮቹ መልካቸውን ቀይረው በመምጣት የለውጥ መንግስቱን ይፈታተኑት ጀመር፡፡ ለአብነትም ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ የአስተዳደር ብልሽቶች፣ የጥላቻ ንግግሮች ተበራክተው ሃገሪቱን ዋጋ እያስከፈሉ ስለመሆኑ ያነጋገርናቸው ምሁራን ያነሳሉ፡፡ ለዚህም ጥሩ ማሳያ ሲሉ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ተቀስቅሶ የነበረውን ጦርነት ይጠቅሳሉ፡፡

ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያቱ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት የሆነው “የብሔር ፖለቲካ የወለደው ልዩነትን የማስፋት በሽታ ነው” ሲሉ ሃሳባቸውን ማጋራት የጀመሩት በዲላ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ ተስፋዬ መኮንን ናቸው፡፡ ከእያንዳንዱ ግጭት በስተጀርባ በሃገር ውስጥም ይሁን በውጪ የሚገኙ የግል ፍላጎታቸውን ማሳካት የሚፈልጉ አካላትን ተጠቅመው የሚሰሩ ኃይሎች መኖራቸውን ተገንዝቦ ለመፍትሄው መሥራት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ሊሆን ይገባል የሚል ሃሳብም አላቸው፡፡

በዚህ በሽታ የታመመው ማን ነው? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ተማረ የሚባለውን ዜጋ ጨምሮ የመፍትሄ አካል መሆን ያለባቸው አመራሮች መሆናቸው ለችግሩ መባባስ አስተዋፅኦ ማድረጉን ያስረዳሉ፡፡ ይህ በመሆኑም የአንዱ አካባቢ መጎዳት የሌላው ጉዳት መሆኑ ተዘንግቷል፡፡ እንደዚህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ ከአንድነት ይልቅ መገፋፋቱን በማጦዝ ነፃ አውጪ ነን የሚሉ አካላት አጀንዳዎቻቸውን ለማስፈፀም ግጭቶች እንዲበራከቱ በር ከፍቷል።

ይህ ግጭት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሲገባ ደግሞ አንዱን ገፍቶ፣ ሌላውን መደገፉ የማይቀር በመሆኑ መንግስት እራሱን በጊዜ በመፈተሽ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ይላሉ አቶ ተስፋዬ መንግስት ፍትህን፣ ሚዛናዊ የመንግሥት አስተዳደር እና ጠንካራ ተቋማትን ለመገንባት የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

አያይዘውም በኢትዮጵያ የሚተገበሩ የፖለቲካ /አስተዳደር/ ሥርዓቶች ለሃገሪቱ በሚመጥን መልኩ ከራሷ የሥልጣኔ ሞዴል የተቃኙ መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ በሃገር ውስጥ የባህል ስብጥርን ስለሚፈጥር ለሃገር አንድነት ወሳኝነት ሲኖረው፣ እንደ ሃገር ደግሞ የሌላ ሃገር ባህል ያላግባብ እንዳይጫን ለማድረግም ያግዛል፡፡

የተረጋጋ መንግሥታዊ ስርዓትን የፈጠሩ እንደ ቻይና ያሉ ሃገራት በዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገታቸው ምክንያት ጠንካራ ተቋም ማቋቋማቸው እና በሕዝብ የሚታመን መንግሥት መስርተው ለስራ የተመቸ ፖሊሲ መንደፋቸውና እንዲሁም ሕዝባቸውን አንድ ማድረግ መቻላቸው ነው ሲሉም አብነት ይጠቅሳሉ፡፡ የሕዝብ አንድነት የሌላቸው ሃገራት ግን በሌላ ሃገር ባህል ከመደቆሳቸው ባለፈ ምድራቸውም የግጭት እና የጦርነት እንዲሁም የአሸባሪዎች መፈንጫ ሊሆን ይችላል፡፡

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች መምህር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሠላምና ደህንነት ጥናት የዶክትሬት እጩ መምህርት ገነት ዘየደ በአንፃሩ የድህነት፣ የግጭት እና የእርስ በእርስ ጦርነት ምንጩ ብልሹ አስተዳደር መኖር ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ማንሳት ይጀምራሉ። ብልሹ አስተዳደር ያለባቸው ሃገራት የተፈጥሮ ሐብታቸውን መጠቀም ቀርቶ ሰብዓዊ መብትን ማስጠበቅ አይችሉም።

ከሁሉም በላይ ግን በሃገራችን ለግጭቶች መበራከት አባባሽ ምክንያት እየሆኑ ያሉት (በብዛት ግን ሲጠቀስ የማይሰማው) የመገናኛ ብዙሃን የተዛባ የዘገባ ሁኔታ ነው፡፡ ሚዲያ እንደ-አጠቃቀማችን ለልማትም ሆነ ለጥፋት የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም የሚሉት እጩ ዶክተር ገነት፣ የሚዘግቡት እያንዳንዱ መረጃ ከሃገር አንድነት ይልቅ ጠብና ጥላቻ የሚሰብኩ መሆናቸው ለግጭት መበራከት አስተዋፅኦ እያደረገ ነው የሚል ትዝብት አላቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሃገሪቱ የሚዲያ ህጎች በአግባቡ አለመተግበራቸው በመሆኑ ከሩዋንዳ የዘር ፍጅት በመማር አፋጣኝ የእርምት እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ፡፡

ይህ ደግሞ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገ የሃገሪቱን ህልውና ከአደጋ በመጠበቅ አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን የሚያደርግ በመሆኑ ከጦርነት ይልቅ ሠላምን፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን የሚሰብኩ እንዲሆኑ መሥራት ከሚመለከታቸው አካላት ይጠበቃል፡፡

ይህን ማድረግ ሲቻል ይላሉ መምህርት ገነት የሃይማኖት፣ የሃገር በቀል እሴቶችንና ቋንቋዎችን በፍትሃዊነት በመጠበቅ አንድነቱን የጠበቀ ማህበረሰብ መፍጠር ያስችላል፡ ፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ አሁን ላይ በስፋት የሚታየው “እኛ እና እነሱ” የሚል መፈራረጅ ከወዲሁ መክስም እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ሌላው በሃገራችን ለግጭት መባባስ ምክንያት ናቸው በሚል በመምህርት ገነት የተጠቀሱት በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያ ዲያስፖራዎች ናቸው። በሰለጠነው የውጭው ዓለም እየኖሩ የሚያንፀባርቋቸው የተጋነነና እውነታን ከግምት ያላስገባ አካሄድ ሃገሪቱን በችግር ማዕበል ውስጥ እንድትዋልል እያደረገ ነው ባይ ናቸው፡፡ በመሆኑም መንግስት ተከታታይና እውነታውን በግልፅ የሚያሳይ መረጃ በመሥጠት እንዲሁም ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት ብዥታውን ለማጥራት መሥራት አለበት ይላሉ።

ምሁራኑ በፌደራል መንግሥቱ እና በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነትን በማመጣጠን የጋራ እሴቶችን መጠበቅ እንደሚገባ ያነሱ ሲሆን ጠንካራ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ተቋማትን በመፍጠር ሁሉን አገልጋይ ስርዓት እንዲሆን የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ አቶ ተስፋዬ በተለይ ለችግሮች ዕልባት ይሆን ዘንድ ሹመኞች ወይም ፖለቲከኞች ከአድርባይነት በመውጣት እውነትን እውነት፣ ሐሰትንም ሐሰት ማለትን መድፈር አለባቸው ይላሉ፡፡ ብዙሃኑ ሹመኛ ሕዝቡን ሳይሆን የበላይ አለቃውን ለማስደሰት መሥራቱ የሕዝብ ጥያቄ መልስ አልባ እንዲሆኑ አድርጓልና የፖለቲካ ልሂቃን ካሉበት ችግር ሊወጡ ይገባል ሲሉ የመፍትሄ ሃሳብ ያሉትን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል በተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆነ ገለልተኛ የሆኑ የፖለቲካ ልሂቃን ትችታቸውም ሆነ ሙገሳቸው ሀቅን የተንተራሰ አለመሆኑ ለፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ እንዳይኖራቸው አድርጓል ባይ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከአጉል አወዳሽነት እና ተቺነት በመውጣት የሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው ይላሉ፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች በህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቅንነት ይጎላል የሚሉት መምህር ተስፋዬ ይህም በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል አለመተማመን በማስፈን ለጥርጣሬ በር እየከፈተ ነው ብለዋል። በመሆኑም መንግሥት የራሱን መዋቅር በመፈተሽ የእርምት እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው በማድረግ ለዘላቂ ሠላም መስፈን ዋስትና ይሆናል፡፡

የፖለቲካ ልሂቃንም ለሕዝብና ለሃገር ታማኝ በመሆን እውነትን ይዘው ለሃገር እድገት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው ሕዝቡም በተገቢ መረጃ ተመስርቶ ችግሮች ሲያጋጥሙ በትክክለኛ መንገድ በማቅረብ እንዲፈቱ መጠየቅ አለበት ሲሉም መፍትሄ ያሉትን ሃሳብ አንስተዋል፡፡

እጩ ዶክተር መምህርት ገነት ዘየደ በበኩላቸው ፖለቲከኞችና ምሁራን ብሶትን በመቀስቀስ ለግጭት ምክንያት ከመሆን መቆጠብ አለባቸው ሲሉ የመፍትሄ ሃሳባቸውን ያነሳሉ፡፡

ያለፈ ጠባሳን ወይም ክፍተትን በማጉላት ከአንድነት ይልቅ መነጣጠልንና መነቋቆርን የሚሰብኩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሚመለከታቸው አካላት ሊሰሩ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሁሉን አካታች በተለይ ህዝቡን ያሳተፈ ውይይት በማድረግ መፍትሄ አመላካች ሃሳቦች እንዲነሱ ማመቻቸት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በመንግስት መዋቅር ሥር የሚገኙትን ጨምሮ ለግጭቶች መበራከት ምክንያት የሆኑ አጥፊዎችን በሃገሪቱ እና ዓለም አቀፍ ህጎች መሠረት ተጠያቂ እንዲሆኑ መሥራት ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ እና አንድነትን የሚያጠናክሩ እንደ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ያሉ ተቋማትን በማጠናከር መፍትሄ አመላካች ውይይቶች በስፋት እንዲካሄዱ ማገዝ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡