በተሻሻሉ ዝርያዎች የታዩ ውጤቶች የምግብ ዋስትናችንን የሚያረጋግጡ ናቸው
በደረጀ ጥላሁን
ንጋት፦ እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ተክሌ፡- እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፦ በክልሉ የሌማት ትሩፋት ሥራ አጀማመር ምን ይመስላል?
አቶ ተክሌ፦ በሲዳማ ክልል ካለው ህዝብ 27 በመቶ የሚሆነው ከሩብ ሄክታር በታች መሬት ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ በዚህ ትንሽ መሬት ሰርቶ ለመጠቀም ስለሚከብድ መፍትሄ መፈለግ አስፈላጊ ነበር፡፡ ከዚህ ሌላ የሥራ ፈላጊው ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የክልሉ መንግስት ስጋቱን ታሳቢ በማድረግ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፓኬጅ ተጠንቶ ወደ ስራ እንዲገባ ወሰነ፡፡ ለዚህም በእንስሳት ዘርፍ ላይ ከተሰራ ውጤታማ ያደርጋል በሚል የታሰቡ ሰባት ፓኬጆች ተቀርጸው ቀረቡ፡፡ በክላስተር፣ በወረዳና በቀበሌ ተለይቶ የቀረበው ፓኬጅ ተቀባይነት በማግኘቱ የንቅናቄ መድረክ ተዘጋጅቶ አርሶ አደሩን በማወያየትና ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ሥራ ከገባን ከሶስት ወር በኋላ የሌማት ትሩፋት በሀገር ደረጃ ተጀመረ፡፡ እኛም ትግበራ ላይ ስለነበርን የያዝነውን እቅድ ከሌማት ትሩፋቱ ጋር በማቀናጀት ቀጥለናል፡፡
ንጋት፦ የተዘጋጁት ፓኬጆች አፈፃፀማቸው ምን ይመስላል?
አቶ ተክሌ፦ የተዘጋጁት ፓኬጆች ሰባት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የወተት ልማት ክላስተር ሲሆን ሰባት ከተማ አስተዳደሮችና 15 የወረዳ መዋቅሮችን የያዘ ነው፡፡ በነዚህም 312 መንደሮች የተደራጁ ሲሆን አንዱ መንደር 120 አርሶ አደሮችን ይይዛል፡፡ አጠቃላይ 37 ሺህ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በዚህም በበጀት አመቱ 102 ሺህ እንስሳትን በማዳቀል 70 ሺህ ጥጆችን ማግኘት የተቻለ ሲሆን 3ሺህ 323 ቶን የወተት ምርት ማግኘትም ተችሏል፡፡ ለወተት ሀብት ልማት ስራው የዝርያ ማሻሻያ፣ የመኖ ልማትና ጤንነትን የመጠበቅ ስራ ለማከናወን ለወረዳና ለቀበሌ አመራር እንዲሁም ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በመሰራቱ ከእቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል፡፡ ሁለተኛው የዶሮ ሀብት ልማት ክላስተር ነው፡፡ በ30 ወረዳዎችና በ7 ከተማ አስተዳደሮች የሚተገበር ነው፡፡ በነዚህም 555 መንደሮች በዶሮ እርባታ ተደራጅተዋል። 66 ሺህ ህዝብ ተሳትፏል፡፡ ሁሉም አርሶ አደር ከአስር ዶሮ በላይ ማርባት አለባቸው። በመንደር ደረጃ ያሉት ደግሞ 25 የተሻሻሉ እና 7 የአካባቢ ዶሮ ማርባት አለባቸው በሚል እየተሰራ ነው፡፡ በዚህም በበጀት አመቱ 4 ሚሊዮን 43 ሺህ የቄብ ዶሮ ማሰራጨት ችለናል፡፡ 375 ሺህ የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ በአመቱ 15 ሺህ 143 ቶን የእንቁላል ምርት ማግኘት የተቻለ ሲሆን ሥራው ተጨባጭ ለውጥ የታየበት ነው፡፡
ንጋት፦ የአንድ ቀን ጫጩት ሥርጭት በሚፈለገው ልክ ተከናውኗል ማለት ይቻላል?
አቶ ተክሌ፦ የአንድ ቀን ጫጩት ሥርጭት እጥረት ነበር፡፡ እንደ ሀገር ኢትዮ ቺክን የሚባል ተቋም ብቻ ነበር የሚያቀርበው። ሀዋሳ የዶሮ እርባታ ማእከል በአሁኑ ጊዜ አዳሬ የዶሮ እርባታ ኢንተርፕራይዝ ወደ ሥራ በመግባቱ 100 ሺህ የሚጠጋ ጫጩት አስፈልፍለን አሰራጭተናል፡፡ ከዚያ ውጪ ከ13 መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆነ ተቋማት ጋር በትብብር ያሰብናቸው ስራዎች ለማሳካት እየሰራን ነው የምንገኘው፡፡ የደብረ ዘይትን ምርምር ማዕከል ጨምሮ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮ-ዮሮ ከተሰኘ ተቋም ጋር በጋራ እየሰራን እንገኛለን ይህ ተቋም በተለይ በከተማችን ውስጥ የጫጩት ማስፈልፈያ ማሽን አስገብቶ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ እነዚህን ተቋማት ተጠቅመን በተለያዩ ቦታዎች ተደራጅተው ከሚያቀርቡ
አካላት 4 ሚሊዮን ጫጩቶችን ማግኘት ችለናል፡፡ አዳሬ ዶሮ እርባታ ኢንተርፕራይዝ ከፍተኛ አቅም ያለው ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ብቻ 130 ሺህ የአንድ ቀን ጫጩት ማስፈልፈል ይችላል፡፡ ይህን በአግባቡ በመጠቀም የእቅዳችንን ግማሽ በራሳችን እንችላለን፡፡ ሌላው በቅርቡ በግብርና ሚንስቴርና በዓለም ባንክ ድጋፍ በሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ውስጥ የተገነባው ሞዴል የዶሮ እርባታ ኢንተርፕራይዝ መመረቁ ይታወቃል። ማእከሉ ከአዳሬ ዶሮ እርባታ ኢንተርፕራይዝ ተፈልፍለው የአንድ ቀን ጫጩት ተረክበው ለሶስት ወር ያሳድጋሉ፡፡ ከዚያም እንቁላል ለመጣል የደረሱ ቄቦችን ለህብረተሰቡ ያከፋፍላል፡፡ በማእከሉ 30 የሚሆኑ ከዩኒቨርስቲ የተመረቁ ወጣቶች ተደራጅተው እየሰሩ ነው፡፡ ከዚህም አርሶ አደሩ እየገዛ ይጠቀማል፡፡ ይኼው ማእከል ስራው ጫጩት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን የዶሮ መኖም ያቀነባብራል። ለዚህም የአካባቢ ምርቶችን በመጠቀም የሚመረተውን የዶሮ መኖ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ያቀርባል፡፡ ይህም አሁን ላይ የሚታየውን የዶሮ መኖ እጥረት የሚቀርፍ ይሆናል፡፡ ከዚህ ሌላ ዳሌ ወረዳ ተመሳሳይ ማእከል በቅርቡ ይመረቃል፡፡ በነዚህ በመታገዝ በ2016 ዓ/ም ያለምንም ችግር እንወጣለን፡፡
ንጋት፦ የሌሎች ክላስተሮች አፈፃፀምስ ምን ይመስላል?
አቶ ተክሌ፦ ሶስተኛው የማር ክላስተር ሲሆን በክላስተሩ 15 ወረዳዎች ታቅፈዋል። በ 15 ወረዳ 30 መንደር ተደራጅተዋል። በእያንዳንዱ መንደር 20 አርሶ አደሮች፣ አጠቃላይ 600 አርሶ አደሮች በማር ልማት ተደራጅተዋል፡፡ አርሶ አደሮቹ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ እንዲሰሩ ተደርጎ ሌሎች አርሶ አደሮች ከነሱ ልምድ እንዲቀስሙ እና የሰሩትን ማሳያ በማድረግ ሰፊ ስራ ተሰርቷል። በአመቱ 39 ሺህ 798 የተሻሻሉ የንብ ቀፎ፣ የሽግግር፣ ዘመናዊ እና የጨፈቃ ቀፎዎች ተሰራጭተዋል። እንዲሁም 1ሺህ 559 ቶን የማር ምርት ማግኘት ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል ሲዳማ ክልል ቡና በስፋት ይመረታል፡፡ ቡና ሲያብብ ለማር ምርት ወሳኝ በመሆኑ እስካሁን አልተጠቀምንበትም ነበር፡፡ ይህን ለማካካስ ቡና በሚመረትባቸው አካባቢዎች በቡና ማሳ ውስጥ የንብ ቀፎ በመስቀል ተስፋ ሰጪ ውጤት ተገኝቶበታል። አራተኛው ክላስተር የዓሳ ልማት ሲሆን በ14 ወረዳዎች እየተሰራ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል ከሀዋሳ ሀይቅ ብቻ የሚመረተው አሳ ዘንድሮ አባያ ሀይቅን ጨምሮ ወንዝ ያለባቸውና ደጋ አካባቢ ያሉ ወረዳዎች ያመርታሉ፡፡ ወንዞችን በመጥለፍ የአሳ ገንዳ በማዘጋጀት የአሳ ጫጩት በማስገባት አርሶ አደሮች አሳን መመገብ እና ለገበያ ማቅረብ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰራበት ነው፡፡ በዚህ አመት 301 የጓሮ የአሳ ኩሬ የተዘጋጀ ሲሆን በዚህም 60 ሺህ የሚሆን የአሳ ጫጩት በማስገባት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። በአባያ ሀይቅ ወጣቶችን በማደራጀት ምርቱን ለማእከላዊ ገበያ እስከማቅረብ ተደርሷል። ዘንድሮ ሎካ አባያ፣ ይርጋለም እና በንሳ ላይ በጓሮ ገንዳ የረቡ አሳዎች ለገበያ ማቅረብ ተችሏል፡፡ አምስተኛው የሀር ልማት ክላስተር ነው።
ቀደም ሲል ምንም ትኩረት ተሰጥቶት የማያውቅ እና በቀላሉ ገቢ የሚያስገኝ ምርት ነው፡፡ በተለይ የገቢ አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አዋጭ መሆኑን በመረዳት በፓኬጅ ተቀርጾ እየተሰራ ይገኛል። በዚህ ስራ 10 ወረዳዎች ተለይተው 19 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የጉሎ ምርት በማምረት 1 ሚሊዮን 312 ሺህ የሀር ትል በማሰራጨት 884 ኪሎ ግራም የሀር ምርት ተመርቶ ለገበያ ቀርቧል፡፡ በዚህ ሥራ 310 ሴቶች በ10 ወረዳዎች ተደራጅተው አንዱን ኪሎ ግራም ከ800 እስከ 4ሺህ ብር እየሸጡ ይገኛል፡፡ ይህም በእቅዳችን መሠረት ተከናውኗል፡፡ የሥጋ ልማት ክላስተር ሌላው ትኩረት ተሰጥቶት የሚተገበር ስድስተኛው ፓኬጅ ነው፡፡ የእንስሳት ዝርያን ለማሻሻል በቂ መኖ የሚያገኙ ከተሞች በወተት ልማት ክላስተር ተደራጅተው እንዲሰሩ በማድረግ፤ ቆላማ አካባቢ በሰፊው እንስሳትን የሚያረቡ ደግሞ ለሥጋ የሚሆኑ ከብቶች፣ በጎችና ፍየሎችን በማርባት አደልበው ለገበያ በማቅረብ ገቢ እንዲያገኙ ተሰርቷል፡፡ ለዚህም የአርሶ አደሩን ግንዛቤ የማሳደግ እንዲሁም መኖ የማቅረብ ስራ ተሰርቷል፡፡ በክልል ደረጃ በስጋ ሀብት ክላስተር ስድስት ወረዳዎች ተለይተው በሁሉም ወረዳዎች በአመቱ 221 ሺህ የዳልጋ ከብት ለማድለብ ታቅዶ 220 ሺህ ማድለብ ተችሏል። በግና ፍየል 523 ሺህ የሚሆኑትን በማሞከት ከእቅድ በላይ ተከናውኗል፡፡ ሰባተኛውና የመጨረሻው የበግ ክላስተር ነው፡፡ በግ ለክልሉ በጣም ጠቃሚና የሀብት ምንጭ ነው፡፡ በተለይ ደጋማ አካባቢዎች ለበጎች እርባታ ተስማሚ ናቸው፡፡ የበጎችን
ዝርያ ለማሻሻል ሥራዎች ተሰርተዋል። የቦንጋና የአበራ የተሻሻሉ ምርጥ ዝርያዎች በማቅረብ በተሰራው ሥራም ቀደም ሲል ከአንድ በግ አንድ ግልገል የሚገኝ ሲሆን በተሻሻሉት ግን ሁለት ግልገል ማግኘት ተችሏል፡፡ በክልሉ አርቤጎና፣ ሻፋሞ፣ ጭሬና ሌሎች አካባቢዎች በአብዛኛው ዝርያቸው የተሻሻሉ በጎችን ያረባሉ፡፡ አሁን ላይ 20 እና 30 በጎችን በማርባት የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህም ደስተኞች ናቸው፡፡ ሥራው በአስራ ሁለት ወረዳዎች እየተሰራ ሲሆን በቅንጅት ከሰራን የተሻለ ውጤት እናመጣለን፡፡ አሁን ላይ 280 አውራ የቦንጋ በግ እንዲሁም የአበራን 300 በግ አሰራጭተን ተጠቃሚ አድርገናል፡፡
ንጋት፦ በተሻሻሉ ዝርያዎች ላይ የህብረተሰቡ አቀባበል ምን ይመስላል?
አቶ ተክሌ፦ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው እንስሳት ብዙ መኖ ይጠቀማሉ፣ ወተታቸውም አይጣፍጥም የሚሉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ነበሩ፡፡ ይሁንና ህብረተሰቡ በተሻሻሉ ዝርያዎች የተገኙ ምርቶችን መጠቀም ሲጀምሩ ጥቅሙን በማየት ሀሳባቸው መቀየር ጀምረዋል፡፡ እንደውም ለእንስሳቱ ዘር መሻሻል አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የናይትሮጂን እና የአባለዘር እጥረት ስለሚያጋጥም ተጠቃሚው ሁሌም እንዲቀርብለት ይጠይቃል፡፡ ይህ ማለት የተሻሻሉ ዝርያዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናችንን እንደሚያረጋግጥልን ህብረተሰቡ ተረድቶታል፡፡
ንጋት፦ የሌማት ትሩፋት ሥራው ካለው የህዝብ ቁጥር ጋር ይመጣጠናል ብለው ያስባሉ?
አቶ ተክሌ፦ ካለን የህዝብ ቁጥር አንፃር በቂ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በተቻለ አቅም ህዝባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እንሰራለን፡፡ በዚህኛው አመት በታቀደው ልክ የፈጸምን ቢሆንም በቀጣዩ 2016 ዓ/ም ያቀድነው ግን ይህን ታሳቢ በማድረግ በእጥፍ አሳድገን አቅደናል፡፡ ይህም ሥራውን ይበልጥ የሚያሰፋውና ያልተዳረሱ አካባቢዎችን በማዳረስ የህዝቡን ተጠቃሚነት እናሳድጋለን፡፡
ንጋት፦ ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለዎት?
አቶ ተክሌ፦ በአካባቢያችን በርካታ ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ ሥራዎች አሉ፡፡ ሥራ ያለው በመንግስት መዋቅር ብቻ ሳይሆን ትልቅ ገቢ የሚያስገኙ በግል ሊሰሩ የሚችሉ አማራጮች መኖራቸው ታውቆ በሌሎች ስራዎችም መሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም በእንስሳት ልማት ዘርፍ መሳተፍ ጠቀሜታው የጎላ ነው። በዶሮ እርባታ፣ በከብት እርባታና ማድለብ እና የመሳሰሉት ሥራዎች አዋጭነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ በተለይ ወጣቶች በዚህ ዘርፍ ቢሰማሩ ይጠቀማሉ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡
ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ተክሌ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ