በተፈጥሮ የሚከሰተውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ለመቀነስ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ጥናትና ምርምር ለማድረግ ማቀዱን ገለፀ

በተፈጥሮ የሚከሰተውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ለመቀነስ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ጥናትና ምርምር ለማድረግ ማቀዱን ገለፀ

ይህ የተገለፀው ቢሮው በዲላ ዩኒቨርሲቲ በመሬት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት ስልጠና በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

የህዝብ ቁጥር ሲጨምር የተፈጥሮ ሀብት እንደሚመናመን የዩኔስኮ ጥናት ያሳያል ያሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ምክትልና የደን ልማት ዘርፍ ኃላፊ ዮሴፍ ማሩ (ዶ/ር) የጌዴኦ ባህላዊ የመሬት አያያዝ ስርዓቱ ከዚህ በተቃራኒ በመሆኑ ነው በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ የተመዘገበው ብለው፤ ይህ ሀገር በቀል ዕውቀት ቀጣይነት እንዲኖረው ከወትሮው ይልቅ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አሁን አሁን በተፈጥሮ እየተከሰተ ያለውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ለመከላከል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ልማት ቢሮ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ጥናትና ምርምር ለማድረግ ማቀዳቸውን ገልፀዋል፡፡

በቡናና እንሰት ልማትና በሌሎች ዘርፎች አርሶአደሩ ውጤታማ እንዲሆን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ለመከላከል በየዘርፉ ካሉት ምሁራን ጋር ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ምክትል ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን