የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ነገ መካሄድ ይጀመራል
የ2018 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ጅማሮውን ማድረጉ ይታወቃል።
በሁለት ምድቦች ተከፍሎ እዚሁ ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ከተሞች ላይ መካሄድ የጀመረው ፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ሳምንት መርሐግብሩን ይዞ ከሁለት ቀናት ዕረፍት በኋላ በነገው ዕለት ወደ ውድድር ይመለሳል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሁለተኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ ይጫወታሉ።
በመጀመሪያው ሳምንት መርሐግብር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሲዳማ ቡና 4ለ1 በሆነ ውጤት የተሸነፈ ሲሆን ፋሲል ከነማ በበኩሉ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 1 አቻ በሆነ ውጤት መለያየታቸው ይታወሳል።
በነገው ጨዋታ በወልዋሎ በኩል በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ቀይ ካርድ የተመለከተው ብሩክ እንዳለ በቅጣት ምክንያት የነገው ጨዋታ ያመልጠዋል።
አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ደግሞ የውድድር ዓመቱን በሽንፈት የጀመሩት ወላይታ ድቻ እና ድሬዳዋ ከተማ እርስ በእርስ ይገናኛሉ።
በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመሩት የጦና ንቦች በመጀመሪያው ሳምንት በመቻል ባለቀ ሰዓት በተቆጠረባቸው ጎል መሸነፋቸው ይታወሳል።
በአሰልጣኝ ይታገሱ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማም ቢሆን በሊጉ የመክፈቻ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ 2ለ0 በሆነ ውጤት መሸነፉ አይዘነጋም።
በመሆኑም ሁለቱ ክለቦች የመጀመሪያ ሙሉ 3 ነጥባቸውን ለማግኘት በነገው ዕለት የሚፋለሙ ይሆናል።
የፕሪሚየር ሊጉ የሁለተኛ ሳምንት መርሐግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም በነገው ዕለት ሲጀምር ኢትዮጵያ ቡና ከነገሌ አርሲ ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ ሲጫወታ ሸገር ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር ደግሞ ከቀኑ 10 ጀምሮ ይገናኛሉ።
ኢትዮጵያ መድን ከ2ኛ እስከ 4ኛ ሳምንት የሚያደርጋቸው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ክለቡ ባለበት የአፍሪካ ሻምፒዮን ሊግ የማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
ሃኪም ዚዬች ወደ ዋይዳድ ካዛብላንካ ለመዛወር ተስማማ
43 ጎሎች 5 ቀይ ካርዶች እንዲሁም 6 የፍፁም ቅጣት ጎሎች በአንድ ምሽት
ግራሃም ፖተር የሲዊዲን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተሾሙ