43 ጎሎች 5 ቀይ ካርዶች እንዲሁም 6 የፍፁም ቅጣት ጎሎች በአንድ ምሽት
በአንድ ምሽት 43 ጎሎች በተቆጠሩበት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሦስተኛ ዙር መርሐግብር አርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ፒ ኤስ ጂ፣ ባርሴሎና እና ኢንተር ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል፡፡
በኤምሬትስ ስታዲየም አትሌቲኮ ማድሪድን ያስተናገደው አርሰናል 4ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል።
ለሰሜን ለንደኑ ክለብ ጣፋጭ የድል ጎሎችን ቪክቶር ግዮኬሬሽ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር፣ ጋብርኤል ማጋሌሽ እና ጋብርኤል ማርቲኔሊ ቀሪ ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል።
መድፈኞቹ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ 100ኛ ድላቸውን ነው ያሳኩት።
ከሜዳው ውጪ ቪያሪያልን የገጠመው ማንቸስተር ሲቲ 2ለ0 ረቷል።
የሲቲዝኖቹን የማሸነፊያ ጎሎች ኤርሊንግ ሀላንድ እና በርናንዶ ሲልቫ አስገኝተዋል።
በተመሳሳይ ከሜዳው ውጪ ከባየርሊቨርከሰን ጋር የተጫወተው የወቅቱ ሻምፒዮን ፒ ኤስ ጂ 7ለ2 በሆነ ሰፊ ውጤት ረምርሟል።
በጨዋታው ዴዝሪ ዱዌ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ከጉዳት የተመለሰው ኦስማን ዴምቤሌም ተቀይሮ በመግባት አንድ ጎል ከመረብ አሳርፏል።
ባርሴሎናም በሜዳው ኦሎምፒያኮስን አስተናግዶ 6ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል።
በምሽቱ ጨዋታ ፈርሚን ሎፔዝ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሀትሪክ መስራት ሲችል ማርከስ ራሽፎርድ ደግሞ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።
በሌሎች ጨዋታዎች ኢንተር ዩኒየን ሴንት ግሎዥን 4ለ0፣ ኒውካስል ቤኔፊካን 3ለ0፣ ፒኤስቪ ናፖሊዮን 6ለ2 እንዲሁም በሩሲያ ዶርትሙንድ ኮፐንሀገንን 4ለ2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ካይራት እና ፓፎስ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።
በአጠቃላይ ምሽቱን በተካሄዱት የሻምፒዮንስሊጉ የሦስተኛ ዙር የመጀመሪያ ቀን 9 ጨዋታዎች 43 ጎሎች ተቆጥረዋል።
በጨዋታ በአማካይ 4 ነጥብ 78 ጎል እንደማለት ነው።
ሌላው በጨዋታዎቹ በርካታ ጥፋቶችም የተሰሩ ሲሆን የዕለቱ ዳኞች 6 የፍፁም ቅጣት ምቶችን ከመስጠታቸው ባሻገር 5 ቀይ ካርዶችን በአንድ ምሽት መዘዋል።
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሦስተኛ ዙር መርሐግብሮች ዛሬ ምሽትም መካሄዳቸውን ይቀጥላሉ።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
ግራሃም ፖተር የሲዊዲን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ በመሆን ተሾሙ
ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን አሸነፈ
ማንቸስተር ሲቲ ኤቨርተንን በማሸነፍ የሊጉ መሪ ሆነ