ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ባሉ ሂደቶች ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመለየት የሚያስችል ስልጠና ተጠናቀቀ

ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ባሉ ሂደቶች ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመለየት የሚያስችል ስልጠና ተጠናቀቀ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከእርሻ ዝግጅት ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ ባሉ ሂደቶች ውስጥ ያሉ ችግሮችን በመለየት፥ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሲሰጥ የነበረ ስልጠና አጋዥ ነው ሲሉ ከተለያዩ ዞኖች የተወጣጡ ተሳታፊዎች ገለፁ።

‎ያገኙትን ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር በክለሉ የታቀደው እቅድ እንዲሳካ የበኩላችንን ሚና እንዲወጡ የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና መምሪያ አሳስቧል።
‎‎
‎ከሰልጣኞች መካከል አቶ እሸታየሁ ዘሪሁን፣ ከምዕራብ ኦሞ ዞን ማጂ ወረዳ የሰብል ልማት ባለሞያ አቶ አደመ አማረ፣ ከቤንች ሸኮ ዞን ሸይ ቤንች ወረዳ የአዝዕርት ሰብሎች ልማት ቡድን መሪ እና አቶ መስፍን ሀይሌ ሸካ ዞን ማሻ ወረዳ የአዝዕርት ልማት ቡድን መሪ እንደገለፁት፥ ስልጠናው ለምርትና ምርታማነትን ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀው ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ ባሉ ሂደቶች ውስጥ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣት ከንድፈ ሀሳብ ጀምሮ በተግባር የታገዘ ስልጠና መስጠት ውጤታማ እንድንሆን ያስችለናል ብለዋል።

‎አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም፥ የበጋ መስኖ ስንዴ በየአከባቢያቸው ከ2014 ዓ/ም ጀምሮ በአነስተኛ ሄ/ር መልማት መጀመሩን ገልፀው አሁን በሽፋንና በምርት መጠን እየጨመረ መምጣቱን ተናግረው በቀጣይ ታች ያለውን ባለሞያ በማሰልጠንና ብቁ በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በቂ እውቀት ቀስመናል ብለዋል ።

‎የደቡብ ምዕራብ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ባለሞያ አቶ ዳንኤል ዘለቀ በዘንድሮ የበጋ መስኖ ከክልል ጅምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በዕቅድ ዙሪያ በመወያየት ከክህሎት አንፃር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በሶስት ዘርፎች የበጋ መስኖ ስንዴን ለማልማት ከማሳ ዝግጀት ጀምሮ ዘር አዘራር፣ የማዳበሪያ መጠን፣ የዘር መጠን፣ የቦይ አወጣጥ በተመለከተ በንድፍና በተግባር ስልጠናዎች መሰጠቱን ገልፀዋል።

‎ከበጋ መስኖ ስንዴ ጋር ተያይዞ አግሮ ኢኮሎጂን መሰረት ያደረገ ዘር ካለመምጣት ጋር ተያይዞ አብዛኛው አከባቢ ላይ ዘር ከተዘራ በኋላ የሚበላሽበት ሁኔታ መኖሩን የገለፁት አቶ ዳንኤል፥ ይህን ችግር ለመቅረፍ ባለሞያው ክህሎት እንዲኖረው መደረጉን ተናግረው፥ ሰርቶ ማሳያዎች ላይ የሚሰሩ ሳይንሱን በጠበቀ መልኩ እንዲተገብሩ በተግባር መታገዛቸው ተናግረዋል።

‎አቶ ዳንኤል አክለው በቀጣይ በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ያሉትን ተግዳሮቶች በሚፈታ መልኩ ስልጠና መስጠት ተናግረው፥ በቀጣይ ከክልል ጀምሮ ዞንና ወረዳዎችና ቀበሌዎች ላይ ይህንን ተግባር ክትትልና ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።

‎የክልሉ ግብርና ቢሮ የሆልቲካልቸር ሰብሎች ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ተስፍዬ ገ/ሚካኤል የተመረጡና ሊሰፋ የሚችሉ ሰብሎችን በመለየት ስልጠና መስጠቱን ተናግረው ለምርታማነት ከስነ ምህዳርና የማሳ ዝግጅት እንዲሁም ከግብዓት ባለፈ የአስተራረስ ዜዴዎች ላይ በአግባቡ ክህሎት እንዲጨብጡ ተደርጓል ብለዋል ።

‎አቶ ይታይ ወ/ትንሳዔ የሚዛን እጽዋት ጥበቃ ክሊኒክ ማዕከል የበሽታ ባለሞያ በበኩላቸው በሰብል ጥበቃ በእውቀትና በክህሎት ባለሞያዎችን መገንባት ከመሬት ዝግጀት ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ በአርሶ አደሩ ማሳ አሰሳ በማድረግ የሚከሰቱ ተባዮችን ለይቶ የመከላከያ እርምጃዎችን እንዲወስድ የሚያስገነዝብ ስልጠና ከልየታ እስከ መከላከል ደረጃ ግንዛቤዎች ተፈጥሯል ብለዋል።

‎በማጠቃለያ መረሀ ግብሩ ላይ የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሳሙኤል አሰፋ ሰልጣኞች ያገኙትን ክህሎት ለልማት ባላሞያዎች በተገቢው በማስጨበጥ በክልል ደረጃ ተግባሩ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።

‎የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ግብርና ቢሮ ለቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ሸካ ዞኖች ለተወጣጡ የግብርና ባለሞያዎች የበጋ መስኖ እና መደበኛ ስንዴ አመራረት ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቋል።
‎‎
ዘጋቢ፡ ዮናስ ወ/ገብሬኤል – ከሚዛን ጣቢያችን