በክልሉ የተጀመረው አማራጭ የቅጣት ውሳኔ በማረሚያ ተቋማት የሚታየውን መጨናነቅ በመቅረፍ ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን አስታወቀ

በክልሉ የተጀመረው አማራጭ የቅጣት ውሳኔ በማረሚያ ተቋማት የሚታየውን መጨናነቅ በመቅረፍ ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን አስታወቀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሳጂን ኤሊያስ በዙ፤ በክልሉ ባሉ ስምንት ማረሚያ ተቋማት ከ10 ሺህ በላይ ታራሚዎች መኖራቸውን ገልጸው በክልሉ የተጀመረው አማራጭ የቅጣት ውሳኔ በማረሚያ ተቋማት የሚታየውን የታራሚዎች ማደሪያ መጨናነቅ በመቅረፍ የምግብና የህክምና ወጪዎችን እንደሚቀንስ ገልጸዋል።

በአማራጭ የቅጣት ውሳኔ የሚቀጡ ግለሰቦች በማረሚያ ተቋም ገብተው ረዥም ጊዜ የፍርድ ውሳኔ ከተሰጣቸው ጋር በመቀላቀል ሌሎች የወንጀል ድርጊቶችን ከመስማት እንዲርቁ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

የሳውላ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ኮማንደር ብርቱካን መንግስቱ፤ የታራሚ ቁጥር አንድ ቦታ እንዳይከማች የመንግስት በጀት እንዲቆጠብና ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት አንጻርም የተሻለ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ታራሚው በተገደበ ሰዓት የራሱን ቅጣት የሚፈጽም በመሆነ በፈጸሙት የወንጀል ድርጊት በመጸጸት ለህግ ተገዢ እንዲሆኑ ያደርጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት አቶ ንጋቱ በቀለ፤ የአማራጭ ቅጣት ፍርድ ቤቶች ቀላል ወንጀሎች በተፈጸሙበት ወቅት የአጥፊውን ግላዊ ሁኔታ፣ ወንጀሉን ለመፈፀም ያነሳሳውን ምክንያት በማገናዘብ እስርን አማራጭ ከማድረግ ይልቅ የግዴታ ስራ ቅጣት የሚጥሉበት ህጋዊ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአማራጭ ቅጣት አፈፃፀም በተለይም የግዴታ ስራ የቅጣት ውሳኔዎች በህዝባዊ ተቋማት፣ በማረሚያ ቤት እንዲሁም በትምህርት ቤቶች አጥፊዎች ቅጣታቸውን ለሀገር የሚጠቅም የልማት ስራ በመስራት እንዲቀጡ ይደረጋል።

ያነጋገርናቸው አማራጭ ቅጣት የተቀጡ ግለሰቦች በሰጡት አስተያየት በተሰጣቸው ውሳኔ መሰረት መጸጸታቸውን አንስተው ወንጀል አስከፊ በመሆኑ ከተመሳሳይ ድርጊት ለመቆጠብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን